ወደ ምእራብ ተመልከቱ (ገብረህይወት ባይከዳኝን እና እጓለ ገብረ ዮሐንስን)
[ያልተኬደው የነጋድራስ ገብረህይወት እና የእጓለ መንገድ]
ክፍል ሁለት
በክፍል አንድ ላይ ገብረህይወት ባይከዳኝን እና በዋናነት ደግሞ እጓለ ገብረ ዮሐንስን ወደ ምእራብ እንድናማትር የሚያሳስቡበት ምክንያት ምእራብ ውስጥ ግን ምን ቢኖር ነው? ምእራብ ውስጥ የተከሰተው እኛ ጋር ግን ገና ያልተከሰተው ነገርስ ምንድን ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተን ነበር የቋጨነው።
እንግዲህ ገብረህይወት ስለ ምእራባዊነት አውሮፓ ውስጥ በትምህርት ሳለ ካየው፣ ካስተዋለው፣ ከታዘበው፣ ካጠናው ተነስቶ ለእኛ ይበጃል ብሎ ባሰበው መልኩ ልንወስደው ልንማረው የሚገባንን ነገር ነው ሊነግረንየሚሞክረው (በአመዛኙ ወደ ፖለቲካ-ኢኮኖሚው በማድላት)። ምእራብ (በገብረህይወት ቋንቋ ፈረንጆች/ኤሮጳዊ አእምሮ) ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግን በግላጭ ወይም በቀጥታ ያብራራው ወይም የተነተነው ነገር የለም። እጓለ ገብረ ዮሐንስ ግን በግላጭ እና በቀጥታ ሊያዋህደው/ሊያስተፃምረው ከሚፈልገው ያሬዳዊ ስልጣኔ ከመተንተኑ በፊት ምእራብ የሚለውን ፅንሰሐሳብ ምንነቱ እና ምእራብ ላይ የተከሰተው ነገር ምን እንደሆነ በስፋት እና በጥልቀት አብራርቶአል።
ነገር ግን እጓለም ቢሆን ይሄ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ብዙ አጥኝዎች ምእራባዊነትን በአሜሪካ ጥላ ከለላ ስር ያለ እና ልዩ መገለጫ ባህሪው ደግሞ አሜሪካ ከምታራምደው ፖሊሲ አንፃር ከሚመለከተው፤ ለምሳሌ ለፀረ-ኮምዩኒስታዊ አንባገነኖች ድርጅቶች ድጋፍ መስጠቷ፣ እስራኤልን መደገፏ፣ በትላልቅ ድንበር ተሻጋሪ ኮርፖሬሽኖቿ አማካኝነት የምታደርገው የኢኮኖሚያዊ ሀብት ወረራ፣ IMFን እንደ የግል መሣሪያ መጠቀሟ፣ በአጠቃላይ በሉላዊነት (globalization) ሰበብ እና ዲሞክራሲን በማስፋፋት ሰበብ የአሜሪካ ኢምፐሪያሊዝም እንዲስፋፋ ማድረጓን አጣቅሰው የሚፀየፏትን/የሚጠልዋትን አሜሪካ ጋር፤ የእጓለ ምእራባዊነት/አውሮፓዊ መንፈስ ምን ዓይነት ግኑኝነት ወይም ልዩነት ይኖረዋል ለሚል ጥያቄ በግልፅ የተብራራ በቂ የሆነ ነገር ስላላስቀመጠ ተጨማሪ ትንታኔ ያስፈልገዋል እላለሁ።
ከፍልስፍና አንፃር ምእራባዊነት ከአብርሆት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ነው። ስለዚህ ምእራባዊነትን በትክክል ለመገንዘብ አብርሆትን መረዳት ግድ ይላል ማለት ነው።
****
በርግጥ ግን አብርሆት ላይ የተከሰተው ነገር ምንድን ነው?
አብርሆት (enlightenment) በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ (በተለይም በምእራቡ ዓለም) ታላቅ ስፍራ የሚይዝ ነው። ሰው (ግለሰብ) ከእርሱ ከራሱ ውጪ ያለ የበላይ ተቆጣጣሪ የሌለው ሉአላዊ አካል (sovereign entity) መሆኑን የተመሰከረበት ዘመን ነው። የአእምሮዉን ልጓም ራሱ ጨብጦ ይዞ በነፃ-ፈቃዱ ራሱን እየገራ ወደሚፈልገው ዓይነት የህይወት አቅጣጫ መጓዝ እንደሚቻለው የተገነዘበበት ዘመን ነው—አብርሆት። በአጭሩ አብርሆት ማለት አመክንዮአዊ-አእምሮ የክብር ማማ ላይ የተቀመጠችበት ዘመን ነው።
አመክንዮአዊ-አእምሮ የክብር ማማ ላይ እንድትቀመጥ ያደረጉ ደግሞ <<አብርሆት ያጎላቸው የምእራቡን ዓለም ፍልስፍና የገመዱ ሦስት ገመዶች አሉ>> ይለናል Isaiah Berlin (The Root of Romanticism)። ፍሬ-ሐሳቡ እንደሚከተለው ነው:-
1. ሁሉም ትክክለኛ ጥያቄዎች በአመክንዮአዊ-አእምሮ አማካኝነት ሊመለሱ የሚችሉ ናቸው የሚል በአመክንዮአዊ-አእምሮ ላይ ያለ መተማመን:- ይህ ማለት ለሁሉም ዓይነት ጥያቄዎች አሁኑኑ መልስ ይኖረናል ማለት አይደለም። አሁን መልስ መስጠት ወይም ማግኘት ባንችል ነገ፤ ነገ ባንችል በሳምንታት ወይም በወራት ጊዜ ውስጥ፤ በሳምንታት ወይም በወራት ጊዜ ውስጥ ባንችል በአመታት፣ በአስር አመት፣ በመቶ አመት..በሆነ ጊዜ ላይ ልንመልሰው እንችላለን። እዚህ እንኳን ባንመልሰው ሌላ ቦታ መልስ ልናገኝለት እንችላለን። አንድ ጥያቄ ሊመለስ የማይችል ከሆነ ግን ጥያቄው ችግር አለበት (በትክክል አልተጠየቀም) ማለት ነው። ይህ ዓይነት በአመክንዮአዊ አእምሮ ላይ ያለው መተማመን ሴኩላሩም ሃይማኖተኛውም የሚስማማበት ነገር ነው። በአብርሆት ዘመን ላይ የነበሩ ሃይማኖተኞች በአመክንዮአዊ-አእምሮ ላይ ያላቸው መተማመን ከፍ እንዲል የሆነው ወደ አብርሆት ዘመን መሸጋገሪያ ወደ ሆነው የህዳሴ ዘመን (Renaissance) መሸጋገሪያ ድልድይ የነበረው ካቶሊካዊ ፈላስፋ ቶማስ አኳይነስ ባመጣው "አመክንዮአዊ-አእምሮአችን ተጠቅመን የምናስገኛቸው እውነቶች እምነት ላይ ደርሰው ውሸት መሆን አይችሉም" የሚል እሳቤ ቀስ በቀስ እያደገ እየሰፋ መጥቶ አብርሆት ላይ ሲደርስ "እውነትን ያለ ምንም ውጫዊ ድጋፍ በአመክንዮአዊ-አእምሮ መርምሮ መፈለግ ይቻላል" የሚል ቅርፅ በመያዙ ነው።
2. ለእነዛ ጥያቄዎች የሚሰጡት መልሶች ደግሞ ልንማራቸው ልናውቃቸው የምንችላቸው (knowable) ናቸው:- ይህ ማለት ለአንዱ ተገልጦ ለሌላው የማይገለጥ፤ ወይም ደግሞ የተመረጡ ጥቂቶች (ህዳጣን ህሩያን) ብቻ የሚያውቁት የሚባል ነገር አይኖርም ማለት ነው። "ፆም ስግደት አሳንሰሃል፣ ፀሎት ትተሃል፤ ስለዚህ ላይገለጥልህ ይችላል" የሚባል ነገር አይሰራም። ተገለጠልኝ የሚል ሰው እንኳ ቢኖር ለሌላው በአመክንዮ ማስተላለፍ መቻል አለበት። አለበለዚያ ተገለጠልኝ ያለው ነገር እውቀት ወይም እውነት ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም። ይህን ሁኔታ Thomas Pain እንዲህ በማለት ይገልፀዋል (ቃል በቃል አይደለም)፣ "ፈጣሪ በሲና ተራራ ላይ ተገልጦ ለሙሴ ተናግሮት ይሆናል፤ ሙሴ እንዲህ አለ ተብሎ ለኔ የሚነገረኝ ነገር ግን የሙሴ ቃል ንግግር እንጂ የፈጣሪ ቃል ንግግር መሆኑ ማረጋገጫ የለም። ፈጣሪ ለሙሴ እንደተናገረው ማረጋገጫ ሊሰጥ የሚችለው ፈጣሪ ራሱ እንጂ ሙሴም ሆነ ከሙሴ ሰማሁ ያለው ሰው ሊሆን አይችልም።" (Thomas Pain, The Age of Reason)
ይህ ለኔ ተገልጦ ለሌላ የማይገለጥ የሚባል እውቀት ሊኖር የማይችልበት ምክንያት ሊፈጠር የቻለው ደግሞ፤ በአብርሆት ዘመን እውቀት ከአንዱ ወደ ሌላው ለማስተላለፍ የሚያስችል ድንቅ ዘዴ (method) በመገኘቱ ነው። ይህ ዘዴ ሊፈጠር የቻለው ደግሞ ግሪኮች ሲጠቀሙበት የነበረው ሎጂክ እና ሒሳብን ወደ ከፍተኛ የእድገት ወለል ያሻገረው እነ ኒውተን እና ላይበኒዝ ያስገኙት ካልኩለስ አንድ ላይ ሲቀናጁ (integration of logic and calculus) ማተማቲከል ሳይንስ (mathematical science) የሚባል አዲስ ዘዴ ሊወለድ በመቻሉ ነው። ይህ ዘዴ ነው እንግዲህ በየመስኩ ያለን እወቀት ከአንዱ ወደ ሌላው መተላለፍ እንዲችል እና ሁሉም ሰውም የተለያዩ የእውቀት መስኮችን መማር እና ማወቅ የሚችል እንዲሆን (ትምህርት ለሁሉም እንዲሆን) ያደረገው።
3. ሁሉም መልሶች እርስ በርሳቸው የማይጣረሱ ወይም ደግሞ የሚስማሙ ናቸው ወይም መሆን አለባቸው:- ይህ ማለት በአንዱ የእውቀት መስክ ላይ የተገኘ እውነት በሌላ የእውቀት መስክ ላይ ከሚገኝ ወይም ከተገኘ እውነት ጋር አይጣረስም ወይም ሊጣረስ አይገባውም ማለት ነው፤ ምክንያቱም እውነት አንድ ነውና። ለምሳሌ በሳይንስ ውስጥ ኬሚስትሪ ውስጥ የሚገኝ እውቀት ፊዚክስ ላይ ከሚገኝ ወይም ሊገኝ ከሚችል ሌላ እውቀት ጋር አይጣረስም ወይም መጣረስ የለበትም።
****
ስነ-ዓለማዊ ምልከታቸውን ተፈጥሮአዊነት (philosophical naturalism) ላይ አድርገው፤ በአመክንዮአዊ-አእምሮ ላይ ባላቸው መተማማን ወይም ፅኑ እምነት የተነሳም ፍልስፍናዊ የሐሳብ ስርዓታቸውን በነዚህ ሶስት የገመድ ዘለላዎች የገመዱ፤ እና ደግሞ አመክንዮአዊ-አእምሮ የግለሰብ ፋክልቲ በመሆኑ በግለሰባዊነት ላይ ባላቸው አተኩሮት የተነሳ በተለያዩ ጊዜያት የተነሱ ፈላስፎች (በዋናነት Bacon, Descartes, and Locke) የአብርሆታዊ-ዘመናዊነት (ወይም በአጭሩ ዘመናዊነት) ጥንስስ ሐሳብ ሊያበጁ እንደቻሉ አብዛኞቹ የፍልስፍና ታሪክ አጥኝዎች የሚስማሙበት ነው። ዘመናውያን ፈላስፎች የሚባሉት ብዙ ቢሆኑም፣ በመካከላቸውም ብዙ ልዩነቶች ያሉ ቢሆኑም፤ ሁሉንም በአንድነት "ዘመናውያን" የሚያሰኛቸው መሰረታዊ ጉዳይ ግን አለ—በአመክንዮአዊ-አእምሮ ላይ ያላቸው ፅኑ እምነት።
ዘመናውያን አሳቢዎች ቅድመ-ዘመናውያን አሳቢዎች እንደ የእውቀት መሳሪያ አድርገው የሚቀበሏቸውን ጭፍን-እምነትን (faith)፣ ትውፊትን (tradition)፣ እና ተአምራታዊነትን (mysticism) አሽቀንጥረው በመጣል የተፈጥሮ እውቀትን ለማግኘት በአፅንኦት የሚቀበሉት በስሜት ህዋሳት አማካኝነት እንደ የእውቀት መንደርደርያነት የሚያገለግለውን ምስለ-አካልን (perception) እና ምስለ-አካላትን ወደ ፅንሰሃሳቦች የሚያቀናጀውን አመክንዮአዊ-አእምሮን ነው። አመክንዮአዊ-አእምሮ ብቸኛው የእውቀት ማግኛ (ተፈጥሮን ለመገንዘብ) መሳሪያ ነው።
እንግዲህ አመክንዮአዊ-አእምሮ ተፈጥሮን ለመገንዘብ የሚያስችለን ሁነኛ መሳሪያ ነው ካልን፤ የአመክንዮ ስነ-እውቀትን (epistemology of reason) ስርዓት ባለው መንገድ የተፈጥሮ ምርምር ስራ ላይ ስናውለው ሳይንስ ይወለዳል። (Stephen Hicks, Explaining Postmodernism) ከስቲቨን ሂክስ እያጣቀስን እንቀጥላለን።
ከዚህ የተነሳም ነው የአብርሆታዊ-ዘመናዊነት አሳቢዎች ዋና ዋና የሚባሉትን የሳይንስ መሰረቶች መሰረት የጣሉት:-
- calculus, Newton and Leibniz
-Principia, Isaac Newton
-System of Nature, Baron D'Holbach
-Treatise on Chemical Elements, Antoine Lavoisier
በሌላ በኩል ደግሞ አመክንዮአዊ-አእምሮ ግለሰባዊ ፋክልቲ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተን፤ የአመክንዮ ስነ-እውቀትን በሰው ተፈጥሮ ጥናት ስራ ላይ ስናውለው ግለሰባዊነት (individualism) የሞራሊቲ እና የፖለቲካ ምሰሶ ሆኖ ይወለዳል። በዚህ ምክንያት ነው የ ጆን ሎክ A Letter Concerning Toleration እና Two Treatises on Government የሚሉት መፃህፍቶቹ በዘመናዊው የግለሰባዊነት ታሪክ ውስጥ እንደ ትልቅ ምእራፍ ተደርገው የሚወሰዱት። እነዚህ ሁለቱ መፃህፍት የሰውን የማሰብ የማሰላሰል አቅምን ከስነ-ምግባራዊ ግለሰባዊነት (ethical individualism) እና የዚሁ ሞራሊቲ ውጤት ከሆነው በሰዎች መካከል ውስጥ በሚኖር ግኑኝነት ጉልበት ማስወገድን፣ ከግለሰባዊ መብት፣ ከእኩልነት፣ የመንግስት ስልጣንን ከመገደብ፣ እና በሃይማኖቶች መካከል መቻቻል እንዲኖር ከሚያደርግ የፖለቲካዊ ስርዓት ፅንሰሐሳቦች ጋር ያዛመዱ ናቸው።
ስለዚህ በአጠቃላይ ግለሰባዊነት እና ሳይንስ
የአመክንዮ ስነ-እውቀት (epistemology of reason) ውጤቶች ሲሆኑ፤ እነዚህ ሁለቱ ስርዓት ባለው መልኩ በተለያዩ የጥናት መስኮች አውድ ላይ ስናውላቸው እጅግ ሰፊ የሆኑ የሐሳብ እና የተግባር ስርዓቶችን ይወልዳሉ ማለት ነው።
ግለሰባዊነት በፖለቲካዊ አውድ
ግለሰባዊነት ፖለቲካዊ አውድ ላይ ስናውለው ሊበራል ዲሞክራሲ (ይሄ አሁን በአውሮፓ በተለይም ደግሞ በአሜሪ ያለው ዓይነት ሳይሆን classical liberalism ተብሎ የሚታወቀውን ነው) ይወለዳል። ከቅድመ-ዘመናዊነት ከነበረው ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ጋር በንፅፅር ብንመለከተው፤ ቅድመ-ዘመናውያን አሳቢዎች ግለሰብን ለማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ወይም ለሃይማኖታዊ የስልጣን ተዋረድ የሚያስገዛ/የሚያስገብር ምልከታ ሲኖራቸው፤ የክላሲከል ሊበረሊዝም አቀንቃኞች የሆኑ ዘመናውያን አሳቢዎች ግን ሰውን በግለሰባዊ ልኬት የሚመመዝኑ እና የእሴት ልኬት አድርገው የሚወስዱትም ግለሰብን ነው። በባስቲያ አገላለፅ፣ <<ህይወት ፣ አእምሮ (faculties) ፣ ምርት (production)—በሌላ አነጋገር ግለሰብነት (individuality)፣ ነፃነት (liberty)፣ እና ንብረት (property)—ነው ሰው ማለት። ... ህይወት፣ ነፃነት፣ እና ንብረት የሚባሉ ነገሮች ሊኖሩ የቻሉት ሰዎች ህግ በማውጣታቸው ምክንያት ሳይሆን፤ ይልቅ በተቃራኒው ህይወት፣ ነፃነት፣ እና ንብረት የሚባሉ ተጨባጭ ሐቆች ስላሉ ነው ሰዎች ህግ እንዲሰሩ/እንዲያወጡ ምክንያት የሚሆኗቸው>> (Frederic Bastiat, The Law)
በክላሲከል ሊበራሎች ዘንድ የሰው ተፈጥሮ ምክኑያዊ እና ነፃ-ፈቃድ ያለው ህልውነት (being) ነው። ስለዚህ ማህበረሰባዊ፣ ፖለቲካዊ፣ እና ኢኮኖሚያዊ ተቋማቱ እርግጠኝነት ባለው የሞራል ህግ—የግለሰብ መብት—ላይ የሚመሰረቱ መሆን ይኖርባቸዋል። ይሄም ማለት ህብረተሰብ እና መንግስትም ለዚህ ሞራል ህግ ተገዢ መሆን ይኖርባቸዋል ማለት ነው። እኤአ በ1787 ዓም በተረቀቀው የአሜሪካ ህገ-መንግስት ላይ ከዋና አርቃቂዎች አንዱ የነበረው James Wilson ይሄን ጉዳይ በጥያቄ መልክ እንዲህ ይጠቀልለዋል፣ <<ሰው [ግለሰብ] ለመንግስት ሲል ነው የሚኖረው ወይስ መንግስት ነው ስለ ሰው የሚቋቋመው? >> (Neoconservativism: an obituary, Bradley Thompson) አሜሪካኖቹ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጡ፤ ህገ-መንግስታዊ ስርዓታቸውን የመንግስትን የጉልበት ኃይል (coercive power) በእጅጉ በሚገድብ እና የግለሰብ ነፃነትን ደግሞ እጅጉን በሚያሰፋ መልኩ ነው የቀረፁት። ስልጣንን በመከፋፈል (dividing)፣ በመለያየት (separation)፣ በመቆጣጠር (checking)፣ እና በማመጣጥን (balancing) ዘዴ ነው ስርዓተ-መንግስታቸውን ያቆሙት።
ለዘመናት የመንግስት የጉልበት ኃይል ዜጎችን ለማንበርከክ እና እንዲታዘዙ ለማድረግ፣ እንደዚሁም ደግሞ ምን ማሰብ መከተል እንዳለባቸው እና እንዴት መኖር እንዳለባቸው የማስፈፀሚያ ስልጣን ሆኖ ነበር የቆየው (አሁንም ድረስ በስፋት የሚታየው እንደዛ ነው)። የአሜሪካ መስራች አባቶች ግን የመንግስትን ስልጣን የሰዎችን መብት ወደ መጠበቅ አጥብበው የግለሰብን ነፃነት በማስፋት ነው የመንግስትን የጉልበት ኃይል በዜጎች ህይወት ላይ ያን ያህል ጣልቃ እንዳይገባ አድርገው ያጠሩት።
***
ሐሳቡን ስንጠቀልለው በአጭሩ፣ በ18ኛው ክዝ ላይ የተከሰተው አብርሆታዊ-ዘመናዊነት በፖለቲካዊ ስርዓት አካሄድ ላይ ያመጣው ከዚህ በፊት ያልታየ አዲስ ለውጥ ቢኖር የህገ-መንህስት ትርጉም በአፍጢሙ እንዲደፋ ማድረጉ ነው። ይህ ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት ከአብርሆት ዘመን ሊቃውንት አንዱ የሆነውና አራተኛው የአሜሪካ ፕረዝደንት James Madison በአሜሪካ ህገ-መንግስት እና በሌሎች አገሮች ህገ-መንግስት መካከል ያለውን ልዩነት አስመልክቶ "Charters" በምትል መጣጥፉ ላይ ያሰፈረውን እንመልከት ። እንዲህ ይላል (ቃል በቃል አይደለም):-
<<የአሜሪካ ህገ-መንግስት ህጉ ከነፃነት [ነፃ ህዝብ] ለመንግስት የተፈቀደለትን የስልጣን ቻርተር የሚደነግግ (charters of power granted by liberty) ሲሆን፤ የሌሎች አገሮች ህገ-መንግስት ግን ህጉ ስልጣን [መንግስት/ባለ ስልጣን] ለህዝብ የፈቀደውን የነፃነት ቻርተር (charters of liberty granted by power) ነው።>>
ይህ ልዩነት መሬት ላይ ወርዶ በተግባር ሲመነዘር የሚፈጠረው ነገር ፓርላማን በምሳሌነት ወስደን ብንመለከተው፤ በአሜሪካው ዓይነት ህገ-መንግስት (ብያንስ የህገ-መንግስቱ መንፈስ) ፓርላማ የሚቋቋመው መንግስትን የሚቆጣጥር ተቋም ሆኖ ነው። በሌሎች አገሮች ህገ-መንግስት ግን ፓርላማ የሚቋቋመው መንግስት ህዝብን የሚቆጣጠርበት መሳሪያ ሆኖ ነው ማለት ነው።
እጓለም የማዲሰንን ሐሳብ የሚደግፍ በችሮታ ስለሚሰጥ ነገር የሚለው አለው:-
<<...ሰው በስጦታ ወይም በችሮታ በሚገኘው ድሎት የማይደሰት መሆኑንና ከገነት ለመውጣት የደፈረው ከእውቀት በሚያገኘው ጉልበት ራሱን ለማስተዳደር የራሱ ባለስልጣን ገዥ ለመሆን ነው እስከ ማለት እንደርሳለን።>> ይህ ሃሳብ በአምላክ ፊትም ቢሆን የሚፀና መሆኑን ለማስረገጥም ፈጣሪ ገነትን የመሰለ ስፍራ እንኳን ለሰው አዘጋጅቶለት እያለ ሰው ግን ገነት ውስጥ፤ በምቾት፣ ግን ደግሞ በባርነት ከመኖር፣ ምቾቱ ቀርቶብኝ በክርስትና አገላለፅ <<እሾህ አሜከላ በሚበቅልባት>> ምድር በነጻነት መኖር ይሻለኛል ማለት እንደሚችል በግጥም መልክ ያስቀምጣል—እጓለ። ሰው ምድር ላይ ሆኖ ገነትን ሲያስብ የሚሰማው ስሜት ለመግለፅም የግጥሙ የመጨረሻው አርኬ እንዲህ የሚል ይዘት አለው፡-
አማልክት መጡና እንርዳህ ቢሉት
ገነት እንዲያገቡት ተስፋ ቢሰጡት
ለቅፅበት ማረከው የስሜት ብርታት
ራሱን ነቅንቆ በኀዘን ትርዒት
“በሐሳብ ብቻ እንጂ የለሽም በውነት
አስታውስሻለሁ በጋለ ምኞት
ገነት ገነት ሀገሬ ገነት
ምን ይሆናል ግና ዋጋሽ ባርነት”
እንግዲህ ገነት ምቾት ቢኖራትም ሰው የሚመኘውና የሚጥረውም ወይም መጣር ያለበት በገዛ ራሱና በዙሪያው ባሉት ነገሮች ላይ ከገዛ ራሱ የሚመነጭ ስልጣን እንዲኖረው ስለሆነ የገነት እሳቤ የባርነትን እንጂ የነፃነት እሳቤን እንደማያሳይ ይጠቁማል—እጓለ።
****
ግለሰባዊነት በኢኮኖሚ አውድ
ግላሰባዊነት በኢኮኖሚ አውድ ላይ ስናውለው ነፃ ገበያን እና ካፒታሊዝምን (laissez-faire) ይወልዳል። የአዳም ስሚዝ በተለምዶ Wealth of Nations በመባል የሚታወቀው መፅሐፍ በይበልጥ ይህን ሃሳብ የሚያብራራ ነው። በፖለቲካ-ኢኮኖሚ ለሁለት ሺ አመታት የበላይነት አግኝቶ የቆየው አስተሳሰብ የፕሌቶ ሐሳብ ነው። ፕሌቶ አንድ ግዙፍ የፖለቲካ-ማህበረሰብ-ህንፃን ለማቆም የተነሳ ማሕበረሰባዊ ኢንጅነር (social engineer)፤አብዛኞቹ ሰዎችን ለህንፃ መስሪያ ግብአት እንደሚሆኑት ብረታ ብረቶች እና ብሎኬቶች አይነት አድርጎ ሊጠቀምባቸው የሚገባ ናቸው ይላል። ይሄ የፖለቲካ-ማህበረሰብ-ህንፃን የመገንባት ስራ የተሳካ እንዲሆን ደግሞ የኢንጅነሩ ፕላን እንጂ የመንጎቹ ፈቃድ ምንም ጥቅም የለውም ይላል።
በ18ኛው ክዘ የተከሰተው አብርሆት ግን ሰዎች በላያቸው ላይ የሚሾም ገዥም ሆነ ተቆጣጣሪ ፖሊስ ሳያስፈልጋቸው ምድርን በምርት ሊያጥለቀልቋት እንደሚችሉ ያሳየ ነው። አዳም ስሚዝ የጫማ ሰሪ ምሳሌ ተጠቅሞ እንዲህ ያብራራል:-
ጫማ ሰሪ ለእኛ አስቦ አይደለም ጫማ የሚሰራው፤ ይልቅ ስለ ራሱ ግላዊ-ጥቅም (selfish-interest) እንጂ። ማለትም እሱ የሚያስፈልገውን ሌላ አይነት ምርት ደግሞ ከሌላው አምራች በንግድ ልውውጥ ማግኘት ስለሚፈልግ እንጂ። ሁሉም ሰው የራሱን ፍላጎት ለማርካት ብሎ ሲሰራ ግዴታ የሌሎችን ፍላጎትንም ማርካቱ አይቀሬ ነው። ይሄ የአንዱን ፍላጎት ሌላው የሚያረካበት መንገድ፤ የሆነ "ገዥ/ንጉስ" ትእዛዝ ማስተላለፍ ሳይጠበቅበት ገበያ ላይ ባለው የሰዎች ራስ-ገዝ (autonomous) የሆኑ ድርጊቶች የሚያከናውኑት ነው የሚሆነው።
ሳይንስ በማቴሪያላዊ ምርት አውድ ላይ ስናውለው ኢንጅነሪንግ እና ቴክኖሎጂ ይወለዳል። ይሄ በአጭሩ ኢንዱስትሪያላዊ አብዮትን ያቀጣጠለ ነው። ሳይንስን የሰዎችን አካላዊ ተፈጥሮ ሁኔታ መርዳት ላይ ስናውለው ህክምና (medicine) ይወለዳል።
****
በእጓለ አገላለፅ ይሄን የሰው ልጅ <<ለብዙ ዘመናት ያህል ተረት (mythos) የሚባል ሸረሪት መሳይ ነገር ድሩን በላዩ አድርቶበት የሚበጠስ መሆኑን ሳያውቅ ተሸፍኖ>> ሲኖር፤ ግሪክ ላይ "የፍልስፍና መቅድም" በሆነው መጠራጠር በተረት የተገነባውን ህንፃ ለማፈራረስ ተነሳስቶ የነበረውን መንፈስ፤ ለብዙ ዘመናት ተዳፍኖ ቆይቶ በኋላ አውሮፓ ላይ በምልአት የተነሳውን ምእራባዊውን የአብርሆታዊ-ዘመናዊነት ትንሳኤ ለመግለፅ ነው እንግዲህ እጓለ <<የመንፈስ ትንስኤ>> ሲል የገለፀው።
ይሄ አውሮፖዊ መንፈስ ከኛ ሁኔታ ጋር የሚያገናኘው ነገር ምንድን ነው ያልን እንደሆነ፤ እጓለ ከሚለው በሰፊው ለመጥቀስ ያክል <<ይህ የአውሮፓ መንፈስ ወይም ስልጣኔ አንድ ጠባይ አለው። በአመጣጡ መሰረት ከቦታው እና ከጊዜው ጋር የተያያዘ ነው። ግን በንፁህ የህሊና ጥረት የተገኘ ጠቅላላ የሰው መንፈስ ሕግ ስለሆነ በሁሉም ዘንድ የሚፀና ነው። እሊህን የህሊና ህግጋት ወይም የስልጣኔ ፍሬዎች ያስገኙት አውሮፓውያን ናቸው። ግን እስያውያንም አፍሪካውያንም በትምህርት የራሳቸው ለማድረግ ይችላሉ። እውቀት ሲባል በጠቅላላ በማናቸውም ሰው ዘንድ በአምሳለ ዘርዕ ያለ ነገር ነው። ያንተም የኔም አይደለም። የሁላችንም ነው። ብቻ አንዱ ቀደም ብሎ ይገልፃቸዋል፤ ያስገኛቸዋል። በዚህኛው እርዳታ ሌላው ደግሞ በተራው በገዛ ራሱ ውስጥ ካለው የእውቀት ምንጭ ይደርሳል። በዚህ ምክንያት የአውሮፓ መንፈስ ያስገኛቸው የስልጣኔ ፍሬዎች በብዙ ሀገሮች ዘንድ በማናቸውም የትምህርት ደረጃዎች የትምህርት ምልዓት (content) ሆኖአል። ...>>
አሁን ጥያቄው ከእጓለ ጋር ሆነን <<የሰውን እግረ ህሊና አንሻፎ የሚያስነክሰውን ድንቁርና የሚባል ሞያሌ ከነ ሰንኮፉ ነቅሎ... ተረት እጅግ አጥብቦት ከነበረው የህይወት መስክ ሰው ወጥቶ እውቀት ከሚያስገኘው የነፃነት ሰፊ ሜዳ ገብቶ እንደልቡ ተዝናንቶ እንዲራመድ አውሮፓውያን ብርቱ የሆነ ፋውስታዊ ትግል አድርገዋል። የዚህ ተጋድሎአቸው ውጤት ለመላው ዓለም ቡራኬ ሆኖአል።>> እንበል ወይስ፤ ከድንቃድንቅ ታሪካዊ ኪነ ህንፃዎቻችን አጠገብ በደሳሳ ጎጆዎች ውስጥ እየኖርን፤ ለሺህ አመታት የማረሻ ዓይነት እንኳን መቀየር ያልቻለ ከእጅ ወደ አፍ (subsistent) የሆነ ኑሮ እየኖርን እያለ፤ ፈረንጆች/ምእራባውያን ራሳቸው አጥንተው የነገሩንን ከዩኒቨርሱ 5% ያክሉን ነው ያጠናነው/ያወቅነው ያሉንን ይዘን እነሱ በሰሩት ሞባይል፣ ቴሌቭዥን፣ ሳተላይት፣ ማህበራዊ ሚድያ ወዘተ እየተጠቀምን <<ፈረንጅ ገና ምኑን አውቆት፤ እስካሁን አውቄዋለሁ ያለው ራሱ ከኛ ሰርቆ ውስዶ ነው>> እያልን በባዶ ኩፈሳ እንኑር?
ወደ ምእራብ ተመልከቱ!
#የመንፈስ_ትንሳኤ
#እጓለ
#ገብረህይወት_ባይከዳኝ
ሰላም
|