ለሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቋጫ የተጀመሩ ጥረቶችና ፋይዳቸው
ግንቦት 25 ቀን 2014 ዓ.ም. የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት በተመደቡት የአፍሪካ ኅብረት ልዩ ልዑክ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ የሚደረገው ጥረት ዘገምተኛ ቢሆንም፣ ጥረታቸው ወደፊት እየገፋ ነው በማለት መናገራቸው በሰፊው ተዘግቧል። የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት በቀናት ልዩነት በመቀሌ ከሕወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን ገ ብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ጋር ሲነጋገሩ መታየታቸው፣ እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር መገናኘታቸው የሰላም ሒደቱ ጉዳይ ትልቅ ቦታ እንደተሰጠው አመላካች እየመሰለ ነው፡፡
አንዳንዶች ከዚህ ተነስተው ጦርነቱን ለማቆም ወደ ድርድር መገባቱን ሲዘግቡ ከርመዋል፡፡ በተለያዩ አገሮች ጭምር ድርድርና ንግግር ተጀመረ እየተባለ ሲነገርም ቆይቷል፡፡ በመንግሥትም ሆነ በሕወሓት በኩል ተደጋግሞ ቢስተባበልም ነገር ግን በኬንያ፣ በሲሼልስና በናይጄሪያ ንግግር ወይም ድርድር መጀመሩን የሚያትቱ ዘገባዎች በተደጋጋሚ ሲዘገቡ ቆይተዋል፡፡
የጦርነቱ ዋና ተዋንያን መንግሥትና ሕወሓት በድብቅ ንግግር ጀመሩ የሚሉ ያልተረጋገጡ መላምቶች ቢወጡም፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አድማሱ የሰፋና የተዋንያኑ ዓይነትም የበዛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ድርድር ከተጀመረ ወይም ንግግር እየተካሄደ ነው ከተባለ ማን ከማን ጋር ነው የሚነጋገረው? እንዲሁም በምን አግባብና በምን ዓይነት ጉዳዮች ላይ ነው የሚካሄደው የሚለው ትኩረት መሳቡ የሚጠበቅ ነው፡፡ እስካሁን ባለው ሒደት በተጨባጭ ማስረጃዎች አስረግጦ ማቅረብ የሚቻለው የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ለመፍታት ድርድር ወይም ንግግር ተጀምሯል ከሚለው መላምት ይልቅ፣ ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት የሰላም ጥረቶች ተጀምረዋል የሚለው ብዙዎችን የሚያሳምን ጉዳይ ሆኖ ይወሳል፡፡
ግንቦት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ሀና ሲርዋ ቴቴ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ባደረጉት ውይይት፣ የሰላም ጥረት ጉዳይ አንዱ አጀንዳ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ ልዩ መልዕክተኛዋ ከአቶ ደመቀ ጋር ከተወያዩ በኋላ፣ መንግሥት ሌላ ዙር ጦርነት እንዳይከሰትና ግጭቱ በሰላም እንዲፈታ የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያደንቁ በይፋ ተናግረው ነበር፡፡ አቶ ደመቀ ከአምባሳደሯ ጋር በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያ መንግሥት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ፅኑ ፍላጎት እንዳለው መናገራቸውም ተዘግቦ ነበር፡፡ ይህን መሰሉ መረጃ ደግሞ የሰሜኑን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት የሚያስችል የሰላም ጥረት ተጀምሯል የሚለውን ግምት የበለጠ የሚያጠናክርም ነበር፡፡
በሳምንቱ አጋማሽ ከፋና ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ የሰላም ጥረት ስለመጀመሩ የተጠየቁት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ የሚከተለውን ነጥብ አስቀምጠው ነበር፡፡
‹‹የኦባሳንጆ ተልዕኮ ግልጽ ነው፡፡ ግጭት ቆሞ ያልተገደበ የረድዔት አቅርቦት ወደ ትግራይ እንዲገባ ማግባባት ነበር ሲሠሩ የቆዩት፡፡ አሁንም ኦባሳንጆ የሚሠሩት ይህንኑ መሆኑን ነው መንግሥት የሚያውቀው፡፡ መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ ያለ ገደብ የረድዔት አቅርቦት እንዲደርስ ቢፈልግም፣ ነገር ግን ሕወሓት ይህን ሲያስተጓጉል ቆይቷል፡፡ በአፋር ክልል ዕርዳታ በስፋት የሚመላለስባቸውንና ለጂቡቲ ወደብ ቅርብ የሆኑ አራት ወረዳዎችን እስካሁን ወሯል፡፡ በአማራ ክልልም የተለያዩ ቦታዎችን በቁጥጥር ሥር እንዳረጉ ናቸው፡፡ ዕርዳታው በተገቢው መንገድ ለትግራይ ሕዝብ እንዳይደርስ ያደረጉት እነሱ ናቸው፡፡ በሌላም በኩል የትግራይ ሕዝብ በዕርዳታ ድርጅቶች ብቻ እየተቀለበ ሊኖር አይችልም፡፡ አርሶ አደሩ ወደ መደበኛው የእርሻ ሥራው መግባት መቻል አለበት፡፡ ኦባሳንጆ ከዚህ አንፃር ነው የማግባባት ሥራ ሲሠሩ የቆዩት፡፡ እኛ የአፍሪካ ኅብረት መሥራችና መቀመጫ አገር እንደ መሆናችን መጠን፣ ኢትዮጵያ ለሰላም ያላትን ፍላጎትና ሰላም እንዲሰፍን የምታደርገውን ጥረት፣ እንዲሁም ይህ ጥረት በተቃራኒው ካለው ወገን እየገጠመው ያለውን ምላሽ አፍሪካዊያን እንዲያውቁም እንፈልጋለን፡፡ ለዚህ ሲባልም የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ የሆኑትን የኦባሳንጆን ጥረት መፍቀድ አለብን፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በናይጄሪያ ከሕወሓት ሰዎች ጋር ተገናኝተው ተደራድረዋል የተባለው መሠረተ ቢስ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንዴ ከሕወሓት መሪ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ጋር አንዴ በስልክ ተገናኝተዋል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹሙ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በሲሼልስ ከሕወሓቶች ጋር ተነጋግረዋል፣ ወዘተ እየተባለ ብዙ ይነገራል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የናይጄሪያ ጉዞ ሁለት ዓላማ የነበረው ነው፡፡ ኢትዮጵያና ናይጄሪያ በአፍሪካ እጅግ ብዙ ሕዝብ ያላቸው ትልልቅ አገሮች ናቸው፡፡ በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ሁለቱ አገሮች ሚናቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ይህንን ሚና የበለጠ እንዴት እናጎልብተው፣ እንዲሁም የአፍሪካዊያንን የጋራ ድምፅ እንዴት እንፍጠር የሚል ነው አንዱ አጀንዳ፡፡ ሁለተኛው ናይጄሪያ ካላት ከፍተኛ የማዕድንና የኢንዱስትሪ ዘርፍ ልማት ልምድ ኢትዮጵያ የምትጠቀምበትን ዕድል ለማመቻቸት ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዞ ከዚህ ውጪ ሌላ ተልዕኮ አልነበረውም፡፡ ሆኖም ከብርሃነ ገብረ ክርስቶስ ጋር ተገናኙ የሚል መረጃ ሲሠራጭ እኔም አይቻለሁ፡፡ ይህ በጣም መሠረተ ቢስ መረጃ ብቻ ሳይሆን ለከፋፋይ ፖለቲካ ተብሎ የቀረበና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ለማድረግ የታለመ የወያኔ ሴራ ነው፤›› በማለት ነው ስለድርድሩ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት፡፡
ከሚወጡ መረጃዎችም ሆነ መላምቶች በሁለቱ የጦርነቱ ዋና ተዋንያን የሰላም ጥረት መጀመሩን መረዳት ቢቻልም፣ ነገር ግን ሁሉም ወገን ጉዳዩን አደባብሶ ማቅረብ እንደመረጠ መገመት ይቻላል ይላሉ ጉዳዩን የሚከታተሉ ታዛቢዎች፡፡ ጅምሩ የሰላም ጥረት በበጎነት የሚታይ ቢሆንም፣ ሁለቱም ኃይሎች በኦፊሴል በዚህ ቦታ፣ በዚህ ጉዳይና ይህን ውጤት ለማግኘት ተወያይተናል ብለው ደፍረው መናገርን እየሸሹ መሆኑን የሚናገሩ በርካታ ናቸው፡፡
ከሰሞኑ መንግሥት 15 ቢሊዮን ብር በጀት ለትግራይ መመደቡን የሚጠቁሙ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡ መንግሥት ያልተገደበ የረድዔት አቅርቦት ወደ ትግራይ እንዲገባ መፍቀዱና በርካታ ቁጥር ያለው የዕርዳታ ጭነት መቀሌ መድረሱም ሲዘገብ ቆይቷል፡፡ አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የፖለቲካ ሰው በቀጣይ ጥቂት ሳምንታት ስልክም፣ መብራትም፣ ባንክና ሌላም አገልግሎት ሊፈቀድ ይችላል ሲሉ ግምታቸውን ያስረዳሉ፡፡ ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲያስረዱም የሚከተለውን ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡
‹‹የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት በሰላማዊ አማራጭ ከመፍታት ውጪ ሌላ ምርጫ እንደሌላቸው ተፋላሚ ወገኖች የገባቸው ይመስላል፡፡ ዓለም አቀፋዊውም ሆነ አገራዊውን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት ጦርነቱን በሰላም የመቋጨት አስገዳጅ ሁኔታዎችን ሁሉም ኃይሎች ተጋፍጠዋል፡፡ እንዋጋ ቢሉና ጦርነትን ቢመርጡ በየትኛው ኢኮኖሚ ነው የሚዋጉት? አገሪቱ እንድትበታተን ካልፈለጉ በስተቀር ከገባንበት ቀውስ የከፋ ቀውስ እንዲፈጠር ካልፈለጉ በስተቀር ሁለቱም ጦርነትን አይመርጡም፡፡ መንግሥትም ሆነ ሕወሓት ጦርነቱ ቆሞ ሰላም እንዲሰፍን አስገዳጅ የሆነ ምርጫ ላይ ወድቀዋል፡፡ ወደ ውጊያ ለመግባት የሚያስችል አማራጭ የላቸውም፡፡ በውጊያ አገሪቱ ከደረሰባት ኪሳራ በላይ እንዲደርስ የሚፈልጉ አይመስልም፡፡ ስለዚህ አማራጭ አጥተው የገቡበትና ያለቀ ጉዳይ ነው እላለሁ ድርድሩ፡፡ ሁለቱም ብዙ ርቀት በድርድሩ ሄደዋል ብዬ ባምንም፣ ነገር ግን የማይመለስበት ደረጃ ላይ እስኪደርሱ ድረስ ይፋ ያደርጉታል ብዬ አላምንም፡፡ አገሪቱ ብዙ ተቃራኒ ፍላጎቶች የሞሉባት ናት፡፡ አሁን ብልጭ ያሉ ፍንጮችን በማየት ከሕወሓት ጋር ድርድር እንዴት ተደርጎ የሚሉ ብዙ ውዝግቦች እየተነሱ ነው፡፡ በመሆኑም ድርድሩ ብዙ ርቀት እስኪሄድ ድረስ የተለየ ኦፊሴላዊ መረጃ ላይነገር ይችላል፤›› ሲሉ ሐሳባቸውን ያጠቃልላሉ፡፡
የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት በድርድርና በሰላም ለመፍታት ጥረት ተጀምሯል ለሚለው ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ማን ከማን ጋር ነው የሚደራደረው? እንዲሁም የድርድር አጀንዳዎቹ ምንድናቸው? የሚለውም ጉዳይ አሁን ትኩረት ስቧል፡፡ አንዳንዶች ከወዲሁ ድርድሩ አንዱን ወገን ወደ ጎን ያለ ነው በማለት ቅሬታቸውን ወደ ማቅረብ እያመሩም ይገኛል፡፡ የድርድሩ ሐሳብ በጎ ቢሆንም ነገር ግን ግልጽነት ባለመታየቱ ዘላቂ መፍትሔ አያስገኝም የሚለው ሙግት እየቀደመ ነው፡፡ ድርድር ከተጀመረ ደግሞ መሰናክል የሚሆኑና የሚያጨቃጭቁ ጉዳዮች ምንድናቸው ለሚለው ነጥብም፣ ብዙዎች መልስ ለማፈላለግ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
ጋዜጠኛና የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ኡመር ረዲ ለሪፖርተር በሰጠው ምላሽ፣ በሰላም ሒደቱ ውስጥ ያሉ ወሳኝ ነጥቦችን ለያይቶ መመልከት እጅግ አስፈላጊ ነው ይላል፡፡ ከወሳኞቹ ጉዳዮች አንዱ ደግሞ ወሳኞቹ ተደራዳሪዎች እነማን ናቸው የሚል ነው የሚለው ኡመር፣ ‹‹ሁለተኛው ከተደራዳሪዎቹ በኩል የሚመነጩ ፍላጎቶች ምንድናቸው የሚለው ይገኝበታል፡፡ በድርድር ሒደቱ ውስጥ ያሉ አካላትን ሥጋትና ተቃርኖ መመልከትም ይጠይቃል፤›› በማለትም ያስረዳል፡፡
ኡመር ሐሳቡን ሲቀጥልም፣ ‹‹ሁለቱ ዋነኛ ተደራዳሪዎች ሕወሓትና የፌደራል መንግሥት ናቸው፡፡ ከሕወሓት ጋር የሚደረግ ድርድር በጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ አለበለዚያ መንግሥት የመደራደሪያ ነጥቦቹን ሕወሓትን በማስገደድ እንዲቀበል በማድረግ ነው መደራደር ያለበት ይባላል፡፡ ይህ ሲባል ግን ብዙ ጊዜ ሰላምን ካለመፈለግ ወይም የጦርነት ነጋሪት ጎሳሚነት ተደርጎ ነው የሚመሰለው፡፡ ሀቁ ግን ይህ አይደለም፡፡ ይህን ዓይነት ሥጋት ብዙ ጊዜ የሚመነጨው ትሕነግን በተጨባጭ ከማወቅና ትሕነግ በድርድር ስም ሊሠራቸው የሚችላቸውን ወጥመዶች ከመገንዘብ የሚመጣ ነው፡፡ ሰላምን ከመጥላት አይደለም ነገሩ የሚመነጨው፡፡ መጨረሻ ላይ ሰላም እንዲመጣ ሁላችንም እንፈልጋለን፡፡ ይህ ውዝግብ በሰላም እንዲቋጭ በግሌ እፈልጋለሁ፡፡ ነገር ግን የትሕነግ ታሪክም ሆነ ዓላማ ሁሌም ከሴራ እንጂ ከቅንነት አይመነጭም፡፡ ሕወሓት ሁሌም ቢሆን ማጭበርበር፣ መሰሪነትና ተንኮል የሞላበት ፖለቲካን የሚከተል ኃይል ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ድርድሩን ወደ ወጥመድነት እንዳይቀይረው መሥጋት ተገቢ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ድርድሩ ሁለቱን ብቻ ያካተተ ነው መባሉም ሥጋት ነው፡፡ ድርድሩ ሌሎችን ካላካተተ፣ በተለይ ደግሞ በትሕነግ ብዙ ጉዳት የደረሰባቸውን የአማራና የአፋር ክልሎችን ካላካተተ አይሳካም እላለሁ፡፡ ድርድሩ ሁሉንም ያላካተተ ከሆነ አንዱን ችግር ፈትቶ ሌላ ችግር ውስጥ መግባት ነው ለመንግሥት የሚሆንበት፡፡ ስለዚህ አጠቃላይ (ኮምፕሪሄንሲቭ) የሆነ የሰላም ስምምነት እንዲኖር ከተፈለገ፣ ድርድሩ የፌደራል መንግሥትና የሕወሓት ብቻ መሆን የለበትም፡፡ የአፋርና የአማራ ኃይሎችም መካተት አለባቸው፤›› ሲል ነው አስተያየቱን ያጋራው፡፡
የሴንተር ፎር ናሽናል ኤንድ ሪጅናል ኢንተግሬሽን ስተዲስ ቲንክ ታንክ ተቋም ዋና ዳይሬክተር የታሪክና የፖለቲካ ተንታኝ የሆነው አቶ ኢብራሂም ሙሉሸዋ በበኩሉ፣ ከሥነ ልቦና ጀምሮ ድርድር የሚጠይቃቸውን መሠረታዊ ምቹ ሁኔታዎች በማብራራት ነው አስተያየቱን የሚሰጠው፡፡
‹‹ጦርነትም እኮ አንዱ አለመግባባትን መፍቻ መንገድ ነው ተብሎ የሚጠቀስ መንገድ ነው፡፡ ነገር ግን በጦርነት አለመግባባትን መፍታት እጅግ አውዳሚና አክሳሪ መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡ በጦርነት አለመግባባቶቻችንን ለመፍታት ብዙ ሞክረን ውድመት አተረፍን እንጂ አልተሳካልንም፡፡ ስለዚህ በሰላማዊ መንገድ ነገሮችን መፍታት ለመቀበል የምንገደድበት ጊዜ ደርሷል ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገሮችን በሰላም አማራጭ ለመፍታት መደረግ ከሚገባቸው ጉዳዮች ደግሞ ዕውቅና መሰጣጠት አንዱ ነው፡፡ አንዱ የሌላውን አስተሳሰብ፣ ችግርና ፍላጎት መረዳት መቻል አለበት፡፡ በዚያም ወገን እውነት ሊኖር ይችላል ብሎ ማሰብ አለበት፡፡ የሌላው ሐሳብ ለምን የተለየ ሆነ ብሎ የራስን ግትርነት አቁሞ ሌላውን ለማድመጥ መሞከር አስፈላጊ ነው፡፡ ሁለተኛው ወሳኝ ነጥብ ደግሞ ማንም ሰው በድርድር ሁሉንም የሚፈልገውን ነገር እንደማያገኝ፣ ሁሉንም ነገር እንደማያጣም ማወቅ አለበት፡፡ ሁሉም ወገን ይህን አምኖ ሰጥቶ ለመቀበል፣ ለግልግልና ለስምምነት ራሱን ማዘጋጀት አለበት፡፡ በጦርነቱ ምክንያት የመጡ መሠረታዊና አስፈላጊ ጉዳዮች ቀድመው መስተካከል አለባቸው፡፡ ሰዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ ማግኘት አለባቸው፡፡ እንዲሁም መሠረታዊ አገልግሎቶች ሊያገኙም ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ሰብዓዊ ቀውስ ባለበት ድርድር ማካሄድ ውጤታማ አይሆንም፡፡ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች መለየት መቻል አለባቸው፡፡ መጀመሪያ ግጭት ማቆም፣ ከዚያ መሠረታዊ ነገሮች ለሰዎች ማሟላት እያለ በቅደም ተከተል ወደ ድርድሩ መግባት ይቻላል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ደረጃ በደረጃ መተማመንን የሚፈጥሩና የድርድሩንም ውጤት የሚያሳኩ ናቸው፡፡ አሁን የግድ መሆን የሌለባቸውን ነገር ግን በዘላቂነት ግጭቱን የሚፈቱና ሊዘገዩ የሚችሉ ጉዳዮችን፣ ተጨባጭ ሁኔታዎችን በመገምገም ማዘግየት ይቻላል፤›› በማለት ነው አቶ ኢብራሂም ሐሳቡን ያሳረገው፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ መኮንን ዘለለው በበኩላቸው የድርድሩን ሒደትም ሆነ የሰላም ጥረቱን ስምረት ከሕወሓት መሠረታዊ ባህሪ በመነሳት ነው የሚገልጹት፡፡ የቀድሞው የሕወሓት ታጋይና አሁን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አማካሪና የበላይ ጠባቂ የሆኑት አቶ መኮንን፣ ሕወሓት ድርድርንም ሆነ ሰላማዊ አማራጮችን እንደማያውቅ ይናገራሉ፡፡
‹‹ከሕወሓት ተፈጥሮአዊ ባህሪ ተነስቼ ድርድርን ቡድኑ እንደ ችግር መፍቻ መንገድ ያውቃል ለማለት እቸገራለሁ፡፡ ሁሌም ቢሆን ጦርነትና ግጭትን የሚፈልግ ኃይል ነው፡፡ አሁንም ከሚያደርገው ነገር ተነስቼ ሰላማዊ መፍትሔውን ይቀበለዋል፣ አምኖበትም ይገዛበታል ብዬ ለመደምደም እቸገራለሁ፡፡ የትግራይ ሕዝብ እየተራበና በጦርነቱ እያለቀ ነው፡፡ ሕወሓት የሕዝቡን መሠረታዊ አገልግሎት፣ የሰላምና የምግብ ጥያቄ ለማፈን የሚፈልገው በጦርነት ነው፡፡ አሁን ህልውናችን አደጋ ላይ ወድቋል፣ ተከበናል፣ በጦርነት ላይ ነን፣ ወዘተ እያለ የሕዝቡን መሠረታዊ ጥያቄ ወደ ጎን በማለት የራሱን የሥልጣን ዕድሜ ማራዘም የሚፈልግ ኃይል ነው ሕወሓት፡፡ ሕወሓት ለራሱ ፖለቲካ ጥቅም አገኝበታለሁ ብሎ ካመነ ብቻ ነው ወደ ድርድሩ የሚመጣው፡፡ ሕወሓት ወደ ድርድር ገባሁ ካለ መሠረታዊ የሕዝቡን ጥያቄ ለመፍታት ሳይሆን፣ አድብቶ ለራሱ የሚያውለው ጥቅምን ማሳካት ይፈልጋል ብዬ ነው የምወስደው፤›› ሲሉ አቶ መኮንን በወጣትነታቸው የተዋጉለት ድርጅት ከመሠረታዊ የጠብ አጫሪነት ባህሪው አለመታረቁን ያስረዱት፡፡
በዩናይትድ ኪንግደም ኬንት ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ብዙነህ ይመኑ (ዶ/ር)፣ ግንቦት 30 ቀን 2014 በአፍሪካን አርጊዩመንት ድረ ገጽ (Ethiopia’s complicated barriers to peace) በሚል ርዕስ ባወጡት ዘለግ ያለ ጽሑፍ፣ ለኢትዮጵያ ጦርነት የሰላም መፍትሔ ለመፈለግ ዕክል የሚሆኑ ወሳኝ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡ የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉትሬስ የሚጨበጥ የሰላም ጥረት ተጀምሯል ማለታቸውን፣ እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት ልዩ ልዑክ ኦባሳንጆ ከሁለቱ ዋና ተፋላሚ ኃይላት መሪዎች ጋር (ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይና ከደብረ ጽዮን ጋር) መገናኘታቸውን ጠቁመው፣ የሰላም ማስፈን ጉዳይ አሁን ዋና አጀንዳ ሆኖ መምጣቱን ጸሐፊው ይገልጻሉ፡፡ የሰላም ጥረቱ በተፈለገው ሁኔታ እንዲሳካ ከተፈለገ ግን መታየት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች መኖራቸውን የሚገልጹት ብዙነህ (ዶ/ር)፣ ጉዳዩ ብዙ ተፃራሪ ፍላጎቶች ያሏቸው ኃይሎች የተሠለፉበት መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ማን ምን ይፈልጋል የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ ደግሞ ከሕወሓት በመነሳት አማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ኤርትራና ሌሎች ኃይሎች የያዙትን አቋም ጸሐፊው ይዘረዝራሉ፡፡
‹‹ሕወሓት በዋናነት ከሚጠይቃቸው ጉዳዮች ውስጥ የአማራና የኤርትራ ኃይሎች ከያዟቸው የትግራይ አካባቢዎች ለቀው ይውጡ የሚል ጥያቄ ይገኝበታል፡፡ ይህ ቀላል ቢመስልም እጅግ ውስብስብ ጥያቄዎችን የሚያስከትል ጉዳይ ነው፤›› ይላሉ ጸሐፊው ሐሳባቸውን ሲቀጥሉ፡፡ ‹‹ሕወሓት የተያዘብኝ ቦታ ይለቀቅ ሲል በምትኩ በአማራም ሆነ በአፋር የያዛቸውን ቦታዎች ለመልቀቅ ዝግጁ ነው ወይ የሚል ጥያቄ ማስከተሉ አይቀርም፡፡
የአማራ ኃይሎች ወልቃይት የሚሉትና ሕወሓት ምዕራብ ትግራይ እያለ በሚጠራው አካባቢ የሚነሳው የይገባኛል ጥያቄ፣ በምን አግባብ እንደሚፈታ በአግባቡ መታየት አለበት፡፡ የኤርትራ የባድመ ይገባኛል ጥያቄም ከዚሁ የሰላም ጥረት ተለይቶ መታየት አይችልም፡፡ በሌላም በኩል በኦሮሚያ የተስፋፋው የኦነግ ሸኔ ኃይል በጦርነቱ ራሱን ተሳታፊ ማድረጉም ሊዘለል አይችልም፡፡ እነዚህን ሁሉ በተፃራሪነት የቆሙ ኃይሎች የሚያስታርቅ የሰላም ጥረት ጦርነቱ ይጠይቃል፤›› የሚሉት አጥኚው፣ ከባድ ቢሆንም ችግሩን የመፍቻ መንገድ ግን መኖሩን ያስቀምጣሉ፡፡ የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋሙና ወደ ሥራ መገባቱ ለዚህ ትልቅ ዕርምጃ ነው የሚሉት ጸሐፊው፣ በሌላም በኩል በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥረትና በነባር ሕገ መንግሥታዊ ሕጎች መፈታት የሚችሉ የወሰን ይገባኛል ችግሮች መኖራቸውን በማመልከት ነው ሐሳባቸውን የሚያጠቃልሉት፡፡
ድርድር ተጀምሯል ወይም የሰላም ጥረቱ ብዙ ርቀት ሄዷል ከሚለው መላምት እኩል ሕወሓትን የሚጠራጠሩ በርካታ ናቸው፡፡ ወደ ድርድር መግባቱንም ሆነ ይህንኑ የድርድር አማራጭ በሀቀኝነት ይጠቀምበታል የሚለው ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ብዙ ናቸው፡፡ ይህንኑ የድርድር ወይም የሰላም ጥረት በተመለከተና ሒደቱ ምን ሊሆን ይችላል ስለሚሉ ጉዳዮች ለሪፖርተር ምልከታቸውን ያጋሩ ምሁራንም ቢሆኑ፣ በዚህ ላይ የተለያዩ ሐሳቦችን ነው ያንሸራሸሩት፡፡
የሕወሓት የቀድሞው ታጋይ አቶ መኮንን ሁሉም የጦርነቱ ባለድርሻ ወገን መደራደር አለበት ይላሉ፡፡ ‹‹ኤርትራም፣ የአማራ ኃይሎችም፣ የአፋር ኃይሎችም፣ የትግራይ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሕወሓትም ሆነ በዚህ ጦርነት ፍላጎቴ ተነክቷል የሚል ወገን ወደ ድርድሩ ቀርቦ መነጋገር አለበት፡፡ የድርድሩ መርህ በሰጥቶ መቀበል መሄድ መቻል አለበት፡፡ ይህን ደግሞ ማሳካት እንችላለን፡፡ ድርድሩ ለሁሉም ነገር መፍትሔ ያመጣል ማለት ላይሆን ይችላል ነገር ግን ተቀራርቦ መወያየቱ ጠቃሚ ሆኖ ይታየኛል፡፡ አሁን ሕዝቡ በየአቅጣጫው ተሰላችቷል፡፡ በጦርነት ለመቀጠል የማይችልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ሕወሓት ሕዝቡ ማምረሩን ተረድቶ በሕይወት መቆየት ከፈለገ ወደ ድርድር ይመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሁሉም ወገን ሕዝቡን እያዋጉ መቀጠል የሚችሉበት ዕድል እየጠበበ ነውና መወያየት አለባቸው፤›› በማለት የተናገሩት አቶ መኮንን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጦርነት የበቃው መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች ማሳየቱን እንደ ዋና የድርድር ገፊ ምክንያት ይጠቅሳሉ፡፡
ጋዜጠኛና የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተንታኝ ኡመር ሐሳቡን ሲያብራራ፣ የሕወሓት አመራሮች ጥቃቱን መጀመሪያ ሲከፍቱ በአደባባይ ጭምር ጦርነቱን ቀጣናዊ እናደርገዋለን ማለታቸውን ያወሳል፡፡ ‹‹ሕወሓቶች ደጋግመው እንደተናገሩት በማንምና በየትኛውም ቦታ ጥቃት እንከፍታለን ብለው ጎንደር፣ ባህር ዳርና ኤርትራ አስመራ ድረስ ጥቃት ሲፈጽሙ ነበር፡፡ የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሥዩም መስፍን (አምባሳደር) ጦርነቱ ከተጀመረ ሌሎች የውጭ ኃይሎች ወደ ጦርነቱ ይሳባሉ ሲሉ ተናግረውም ነበር፡፡ የእነሱ ቀመር ኤርትራን ከዚያም ቀጥሎ ሱዳንን ወደ ጦርነቱ ማስገባትና ጦርነቱን ዓለም አቀፋዊ ማድረግ ነበር፡፡ ይህ ፍላጎታቸው ደግሞ አሁንም ድረስ አልተለወጠም፡፡ ከሰሞኑ ከኤርትራ ጋር የሚያደርጉት ግጭትም የዚሁ ጥረት አካል ሆኖ መቅረብ የሚችል ነው፡፡ ጦርነቱን ትሕነግ ቀጣናዊ ለማድረግ የሚፈልገው ደግሞ አንደኛ ከፌደራል መንግሥት እኩል ራሱን ተገዳዳሪ አድርጎ ለማቅረብ ባለው ፍላጎት ነው፡፡ በእኔ ግምት ግን ማንኛውም ክልል ከፌደራል መንግሥት እኩል ራሱን አተልቆ ማቅረብ አይችልም፡፡ በወታደራዊ፣ በውጭ ግንኙነት፣ በኢኮኖሚም ሆነ በፋይናንስ የፌደራል መንግሥቱን ክልሎች መገዳደር አይችሉም፡፡ ትሕነግ ራሱ የሠራው አከራካሪው ሕገ መንግሥት ራሱ ይህንን አይፈቅድም፡፡ ከትሕነግ ጋር የመደራደሩን ሒደት አስቸጋሪ ከሚያደርገው ጉዳይ አንዱ ይህ ነው፡፡ ራሱን ከፌደራል መንግሥት ጋር እኩል አድርጎ ይቆጥራል፡፡ ራሱን ክልል አድርጎ ማቅረብ ሲገባው በአንድ ሉዓላዊ አገር ውስጥ እንዳለ ራሱን የቻለ መንግሥት ራሱን ቆጥሮ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጭምር በውጭ ጉዳይ በኩል እያለ ደብዳቤ ለመጻፍና እንደ ነፃ መንግሥት ራሱን እየሳለ ሲያቀርብ ታይቷል፡፡ አሁን ከኤርትራ ጋር የሚደረገው ትንኮሳም የዚሁ ፍላጎቱ አካል ነው፡፡ በኤርትራ በኩልም ሆነ በሱዳን በኩል ያሉ ፍላጎቶችን ትሕነግ በግሉ የሚጨርሰው ሳይሆን የአገር ጉዳይ ናቸው፡፡ ድርድሩ መሆን ካለበት ደግሞ ትሕነግ እንደሚፈልገው የአሜሪካ ወይም የአውሮፓ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትልቅ ድርሻ እንዲኖራቸው ከማድረግ ይልቅ፣ የአፍሪካ ኅብረት ዋና ተዋናይ እንዲሆን መደረግ ነው ያለበት፤›› ብሏል፡፡
የታሪክ ተመራማሪና የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ኢብራሂም በበኩሉ፣ የግጭቱን ባለድርሻዎች በሁለት መንገድ የአገር ውስጥና የውጭ ኃይል ብሎ መክፈል እንደሚቻልና በዚሁ አግባብ ማደራደር እንደሚበጅ ይናገራል፡፡ ‹‹የውጭ ኃይሎች ጣልቃ የሚገቡት የአገር ውስጥ ተፋላሚዎች ልዩነታቸውን በሰላም መፍታት ሲያቅታቸው ነው፡፡ ለእኔ በጣም አስፈላጊ ነው የምለው የውስጥ ኃይሎች ቅደም ተከተል ባለው መንገድ፣ አንዳቸው ሌላቸውን ለማድመጥ ወስነው ግጭታቸውን በሰላም መፍታታቸው ነው፡፡ በመሠረታዊነት የኢትዮጵያን ችግር ከፈታን ከውጭ የሚመጣ ችግርን እንፈታለን ማለት ነው፡፡ ጦርነት ለማንም እንደማይበጅ ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ሰላም ደግሞ አካታችነትን ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ የሚደረገው የሰላም ጥረት አንዱን አካቶ ሌላውን አግልሎ መሆን የለበትም፡፡ ከሰማይ በታች ያሉ ችግሮች በሙሉ በሰላም ይመለሳሉ፡፡ አገራችን የተለየች ናት ብለን ማሰቡም ሆነ የገጠመንን ችግር የተለየ አድርጎ መመልከቱ አይበጅም፡፡ ሁሉም መሣሪያውን ወደ ጎን ብሎ ለሰላም መቀመጥ አለበት፡፡ ብዙ ችግሮቻችን ከብዝኃነትና ከልዩነት የሚመነጩ ናቸው፡፡ ብዝኃነትን ለመሸከም የሚያስችል መፍትሔ በሰላም ለማግኘት ነው መጣር ያለብን፡፡ ችግራችንን በእኛው መፍታት እንደምንችል አምነን የውጭ ኃይሎችን መጋበዝ ጣጣ እንዳለው አውቀን በራሳችን ችግራችንን መፍታት እንችላለን ብዬ አምናለሁ፤›› በማለትም አቶ ኢብራሂም ያስረዳል፡፡
ግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም. አሜሪካ የኢትዮጵያን ጦርነት ለመፍታት በሚደረገው የሰላም ሒደት ስለሚኖራት ሚና “Optimizing U.S. Strategic Policy: A Regional Approach to Ethiopia” በሚል ርዕስ ሰፊ ዘገባ ያስነበቡት አንድሪው ሉንድና ዊል ተርነር፣ ቀጣናዊ መፍትሔ ፍቱን አማራጭ መሆኑን አስቀምጠዋል፡፡ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የዕርዳታና የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንደ ማስገደጃ በመጠቀም፣ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን የኢትዮጵያን መንግሥት መጫን ትችላለች ይላሉ ጸሐፊዎቹ፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው የዓለም ወቅታዊ ሁኔታ አሜሪካ በዩክሬንና በሩሲያ ጦርነትና በሌሎች ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች የተወጠረች በመሆኑ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በቀጥታ እጇን ብታስገባ የጊዜና የሀብት ብክነት ነው የሚሆንባት ሲሉም ያሳስባሉ፡፡ ከዚህ ይልቅ አሜሪካ በአኅጉራዊው የአፍሪካ ኅብረት ተቋም በኩል ለተጀመረው የሰላም ጥረት ድጋፍ ማድረጉ ነው የሚሻላት ሲሉም ይመክራሉ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያን ጦርነት በቀጣናዊና በአኅጉራዊ ድርጅት መፍታት ከተቻለ ለዓለም ጭምር አዲስ ማስተማሪያ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ የአሜሪካ መንግሥት አኅጉራዊውን የሰላም ጥረት በመደገፍ በኢትዮጵያ ጉዳይ ቀጥተኛ ኃላፊነትን መውሰድም መቆጠብ አለባት፡፡ ከሀብት ብክነት መላቀቅና በሌሎች ወሳኝ በሆኑ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይሻለዋል፤›› በማለት ሁለቱ ጸሐፊዎች ባወጡት ጽሑፋቸው ምክረ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
ኡመር ይህን በተመለከተ ሲናገር፣ ‹‹ትሕነግ የራሱን ፍላጎት ለመጫን ሲል የመንግሥትን አንገት ሸምቀቆ ውስጥ የሚከት ጥያቄ ያነሳል፡፡ በተለይ ከአማራና ከአፋር ክልሎች ጋር በተያያዘ ሕወሓት ችግሮችን የሚያወሳስቡ ጥያቄዎች ማቅረቡ የሚጠበቅ ነው፡፡ ትሕነግ ከሚያሰማው የተበደልኩ ፕሮፓጋንዳ፣ የተወረርኩ ፕሮፖጋንዳና የፀረ ኢትዮጵያ ፕሮፖጋንዳ መረዳት የሚቻለው ይህንኑ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት የትሕነግ ሸምቀቆ ውስጥ ራሱን ላለማስገባት መንግሥት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡ ትሕነግ የድርድር ሒደቱን የማጓተትና ዓለም አቀፍ የሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲገባ የማድረግ ፍላጎት ሊኖረው ይችላል፡፡ በተለይ የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው ድንበሮች አካባቢ ዓለም አቀፍ የሰላም አስከባሪ ኃይል ግፊት የሚያደርገው፣ በእነዚህ የድንበር አካባቢዎች እንደ ልብ የራሱን የውጭ መተላለፊያ መንገድ ለማስከፈትና በዚህም ተጠቅሞ የራሱን ነፃ አገር ፈጠርኩ ለማለትም ሊሆን ይችላል፤›› ሲል ነው ሐሳቡን የሚያጠቃልለው፡፡
አቶ ኢብራሂም፣ ‹‹በመጀመሪያ ደረጃ የራሳችንን ችግር ራሳችን በራሳችን እንፈታለን ብሎ ማመን ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መሠረታዊ የሆነው ጉዳይ ሁሉም ጥያቄ የሚያቀርብ አካል የተለየና የወጣ አመለካከት ነው ብለን ከማውገዝና ሰይጣናዊ ከማድረግ መቆጠብ አለብን፡፡ አላስፈላጊ ቃላትና ውግዘት ሳንጠቀም፣ ነገሮችን ሳናጣምምና ሳንኮንን በጎ በሆነ መንገድ ጥያቄዎችን መቀበልና ለመፍታት ከጣርን መፍትሔ እናገኛለን ብዬ አስባለሁ፤›› ሲል ነው ወደ ራስ ማተኮርን የሚያብራራው፡፡
የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ (ዶ/ር) ድርድርና የመንግሥት አቋም ያሉትን ወሳኝ ጉዳይ ሲያስቀምጡ፣ ‹‹መንግሥት የትኛውም ዓይነት ግጭት በኃይልና በጉልበት ይፈታል ብሎ አያምንም፡፡ በየትኛውም ዓለም ቢሆን ሁሉም ዓይነት ግጭቶች የመጨረሻ መቋጫቸው ውይይት፣ ድርድርና ሰላም ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በታሪክም የለም፡፡ ከዚህ አንፃር መንግሥት ለሰላም ሁሌም በሩ ክፍት ነው፡፡ የትኛውም አካል በሰላም ለመንቀሳቀስ እፈልጋለሁ ካለ መንግሥት ጥያቄ የሚያቀርብበት ምክንያት የለም፡፡ የእኛ መንግሥት የጦርነት ተንኳሽ ሳይሆን የሰላም፣ የልማትና የዲሞክራሲ መንግሥት ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ለሰላም ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ሆኖም ይህን ለማድረግ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚሠሩ ኃይሎች፣ የኢትዮጵያን አንድነት ከማይቀበሉ ኃይሎች፣ ጽንፈኝነትና አክራሪነት በኢትዮጵያ እንዲጎላ ከሚፈልጉ ኃይሎች፣ ኅብረ ብሔራዊነትና ወንድማማችነትን ከማይፈልጉ ኃይሎች ጋር አብሮ አይሠራም፡፡ ይህን ቅድመ ሁኔታ ከማይቀበሉ ከየትኞቹም ኃይሎች ጋር አይደራደርም ማለት ነው፡፡ ኅብረ ብሔራዊነት፣ ወንድማማችነት፣ የሕዝቦች ብልፅግና፣ የሕዝቦች ክብር፣ የሕዝቦች ሉዓላዊነትና የአገሪቱ አንድነት በፍፁም ለድርድር የሚቀርቡ አይደሉም፡፡ ይህ የመንግሥት ፅኑና መታወቅ ያለበት አቋም ነው፤›› ብለዋል፡፡
|