INFORMATIE EN GEGEVENSVERZAMELING VOOR ONAFHANKELIJKE TIGRAY

ኣብዚ ገጽ እዙይ ብተጋሩ ልተጽሓፈ ተግንዩ

ዝርዝር ኣዋርሕ ኣብ ጎኒ እኒሀኩም። መጀመርታ ወርሒ ምረጹ ድሕሪኡ ልትደልዩዎ ኣረስቲ (ጽሑፍ) መሪጽኹም ኣንብቡ።

ስለ ወቅቱ የትግራይ ማእከላዊ ኮማንድ ከፍተኛ አመራር ታጋይ ጌታቸው አሰፋ፤

ስለ ወቅቱ የትግራይ ማእከላዊ ኮማንድ ከፍተኛ አመራር ታጋይ ጌታቸው አሰፋ፤ በተለይም ለኢትዮጵያውያን የቀረበ፤ ተጋሩ ስለሚያውቁት ነው!

ክፍል ሁለት

«ዶሴኛው» ጌታቸው ኣሰፋ፤ ምን ማለት ነው?

«… ጌታቸው ‘ዶሴኛ’ በመሆኑ ነው በበርካቶች ዘንድ እጅግ ተፈላጊ የሆነው፡፡ በአዋጁ አንቀፅ 8 ንዑስ አንቀፅ 1 እስከ 6 በተዘረዙት የመረጃ (Intelligence) ስልጣንና ተግባራቱ ምክንያት ነው ጌታቸው በምስራቅ አፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ እጅግ ተፈላጊ ሰው የሆነው፡፡ በተለይም በዚህ አንቀፅ 8 መሰረት የተጣለባቸውን የሃገርና የሕዝብ ከፍተኛ አደራ ለመወጣት ሲሉ፤ ጌታቸውና የስራ ባልደረቦቹ መፈንቀል ያለበትን ድንጋይ፣ መቆፈር ያለበትን ጉድጓድ፣ መጠለፍ ያለበትን መረጃ፤ ብቻ ምን አለፋህ ህይወታቸውን ሳይቀር ለአደጋ በማጋለጥ፤ የግል ኑሯቸውን አሽቀንጥረው ጥለው፤ ለማድረግ አይደለም ለማሰብ የሚከብዱ ሃገራዊ ጀብዱዎችንና ገድሎችን ፈፅመዋል፡፡

… የእነ ጌታቸው የመረጃና ደሕንነት ተቋም ዋናውና ኣልፋ ኦሜጋ ሃላፊነቱና ተግባሩ፤ ለአገር ደሕንነትና ሰላም፣ ሕገመንግስታዊ ስርዓቱንና የዜጎችን ሰላምና ደሕንነት ለማስከበር፤ የክትትል የማጣራት መረጃና ማስረጃ የማሰባሰብና፤ ለእርምት እርምጃ በጠቅላይ ሚንስትሩ ለሚመራው ለአስፈፃሚው አካል ማቅረብ ነበር:: ሃገሪቱና ሕዝቦቿ ባለፉት በርካታ ዓመታት የተነፈሱት የሰላምና መረጋጋት አየር፣ ተጨባጭ የልማትና የዕድገት ተስፋ፣ ከአፍሪካ አልፎ ዓለምአቀፍ ከበሬታና ወዳጅነት ወዘተ... የዚህ ሃገራዊ ጀብድ ትሩፋቶች ናቸው፡፡

… እንግዲህ በዚህ ሂደት ውስጥ ከአሸባሪና ሙሰኛ ግለሰብ ቡድንና ድርጅት አንስቶ፤ እስከ የመረጃና ደሕንነት ተቋማትና መንግስታት ድረስ፤ በበጎም ሆነ በመጥፎ መተባበር፣ መነካካትና መጠላለፍ የመረጃና የደሕንነት ስራ የግድ ይለዋል፡፡ በዚህም ሂደት ግንባር ቀደሙ ተዋናይ ‘ዶሴኛው’ ጌታቸው ነበር፡፡ በዚህም ሂደት ከግለሰብ ቡድንና ድርጅት አንስቶ እስከ መንግስታትና ተቋማት ድረስ የእያንዳንዳቸውን ዝርዝር ዶሴ በተመለከተ ጌታቸው የማያውቀው የለም፡፡ እያንዳንዱ ዶሴም በዝርዝር የሰነድ ብሎም በድምፅ ማስረጃ የተጠናቀረ ነው፡፡ እነዚህ ዶሴዎች ውስጥ ዘር ብሄር ሃይማኖት ፆታ ሳይለይ ያልተካተተ ሙሰኛ የኢትዮጵያ ባለስልጣንና ባለሃብት አይገኝም፡፡ በርካታ ሙሰኛና በሃገሪቱ ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚና የፖለቲካ አሻጥር ሲፈፅሙና ሲያስፈፅሙ የነበሩ፤ አሁን ሃገሪቱን እየመሩ ከሚገኙ ከፍተኛ የመንግስት አመራር ባለሥልጣናት አንስቶ፤ ባለሃብቶች እያንዳንዳቸው የደለበ ዶሴ አላቸው፡፡

… ከእነዚህ ሙሰኛና በሃገሪቱ ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚና የፖለቲካ አሻጥር ሲፈፅሙና ሲያስፈፅሙ ከነበሩ ባለሥልጣናትና ባለሃብቶች በተጨማሪ፤ በሽብር ተግባር ላይ ተሰማርተው የነበሩና የእነሱ አስተባባሪና አደራጅ የነበሩ፤ እንደኤርትራና ግብፅ የመሳሰሉ መንግስታት ከተባባሪዎቻቸው ጋር፤ እንዲሁም ከዓለምአቀፍ የፀረሽብር ተሳትፎኣችን ጋር በተያያዘ ዓለምአቀፍ ሽብርተኞችና የእነሱ ተባባሪና ደጋፊ የነበሩ የአካባቢው መንግስታትና ተቋማት፤ እነዚህ ሁሉ ባለዶሴዎች ናቸው፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ጌታቸውን በህይወት ይፈልጉታል፡፡

«… ጌታቸው ስለእነዚህ ሁሉ ዶሴ እንዳለው በምን አውቀው ነው ሊያጠፉት የፈለጉት?» የሚል ጥያቄ መነሳቱ ተገቢ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ስልጣኑና ተግባራቱ ጌታቸውና የስራ ባልደረቦቹ መረጃ ማሰባሰብና ለተግባራዊ እርምጃ ለሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ብሎም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚመራዉ የሃገሪቱ ብሄራዊ የፀጥታ ምክር ቤት ማቅረብ ነበር፡፡ እንግዲህ እዚህ ላይ ነው ከፍተኛ የሃገር ክህደት በሃገሪቱ መሪዎች የተፈፀመው፡፡ በተለይም አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝና አቶ ደመቀ መኮንን ከተባባሪዎቻቸው ጋር በኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ላይ ከፍተኛ ክህደት በመፈፀም በሃላፊነታቸው በእጃቸው ውስጥ የገባውን የሃገርን ሰላም፣ ፀጥታ፣ ደሕንነትና ጥቅሞችን የሚያስከብረውንና የሚያስጠብቀውን መረጃ አሳልፈው ለግለሰቦችና ቡድኖች ብሎም እስከ የምስራቅ አፍሪካ አሸባሪው ኢሳያስ አፈወርቂ ድረስ መተንፈሳቸው፤ ታሪክ ይቅር የማይለው ከፍተኛ ክህደት ፈፅመዋል፡፡ አቶ ሃይለማርያምን ተክቶ ስልጣን የተረከበው የወቅቱ ቡድንም ይህንን የተከማቸና እነሱንም እንደግለሰብ የሚመለከት መረጃ ከሌሎች አምሳያዎቻቸው ባለዶሴዎች ጋር እንዲተባበሩና፤ በሃገሪቱ ክብርና ጥቅም ላይ በመረማመድ ከውጭ መንግስታትና ተቋማት፣ በተለይም ከግብፅ ኤርትራና እነዚህን በበላይነት ከሚመሩትና ከሚደጉሙት ሳውዲ ዓረቢያና ኢምሬትስ ጋር ሊያሰልፋቸው ችሏል፡፡

… ይኸው ነው ሚስጥሩ! ዶሴኛው በስልጣን ላይ የነበሩና አሁንም ያሉ የእያንዳንዳቸውን የኢሕአዴግ ሙሰኛ ባለሥልጣናትና ተባባሪ ባለሃብቶችን፤ እንዲሁም የሃገር ውስጥና የውጭ አሸባሪዎችንና ተባባሪዎቻቸው የሆኑ መንግስታትንና ተቋማትን ዝርዝር ዶሴ በመያዙ ነው፤ ተቀናጅተው በህይወት እየፈለጉት የሚገኙት፡፡ እንጂ ጌታቸውና እሱ የመራዉ የብሔራዊ መረጃና ደሕንነት አገልግሎት መስሪያቤት፤ እንደተቋም በአንቀፅ 8 መሰረት መረጃ ከማሰባሰብና ለእርምት ለአስፈፃሚው አካል ከማቅረብ፤ በአንቀፅ 9 መሰረት የሃገሪቱን ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ዲፕሎማቶች፣ የመንግስታት መሪዎችን፣ ሌሎች የሃገሪቱን እንግዶችና እንደ አየርመንገድ የመሳሰሉ የተቋማትን ደሕንነት ከማስጠበቅ ያለፈ ሌላ ተግባር አልነበረውም፡፡

… ይህ የመረጃና የደሕንነት ተቋም አሁን በፈጠራ እንደሚነገርለት የሚያስተዳድረው እስርቤትም ሆነ የምርመራ ተቋም አልነበረውም፡፡ በጣም የሚገርመው ጌታቸውም ሆነ የስራ ባልደረቦቹ እንኳንስ እስረኛ ሊመረምሩና የሰብኣዊ መብት ጥሰት ሊፈፅሙ እስር ቤት በር ላይም ደርሰው አያውቁም:: ይህንን ሓቅ እኔው እራሴ የማውቀውና የማረጋግጠው ነው - ጌታቸው እስር ቤት በር ላይ ደርሶም ሆነ እስረኛን አይቶ አያውቅም:: እነዚህ አሁን በቡድን ሆነው ሃገር በመምራት ላይ የሚገኙት ባላዶሴዎች፤ በተዋረድ በተቋሙ ውስጥ በተለያየ እርከን ለበርካታ ዓመታት በቀጥታና በተባባሪነት ሲሰሩ የነበሩ ስለሆነ፤ የተቋሙን ውስጡን እሰራሩን ሁሉ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡

… እነዚህ አሁን በስልጣን ላይ ያሉትና ተባባሪዎቻቸው የአገር ክህደት ሲፈፅሙ ለመኖራቸው በርካታ መረጃዎች በመረጃና የደሕንነት ተቋም ተጠናቅሮ ለወቅቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማርያም ደሳለኝና ለብሄራዊ ደሕንነት ምክርቤት ቀርቦ ነበር:: በተለይም የአዲስ አበባ አካባቢን የኦሮሚያ መሬት በባለስልጣናትና ባለሃብቶች ቁርኝት መቀራመትን አስመልክቶ፤ ይህንን ወንጀል የሚፈፅሙት እነማን እንደሆኑ ዝርዝር መረጃ ቀርቦ ነበር:: ይህንን በባለስልጣናትና ባለሃብቶች እየተካሄደ የነበረ ዘረፋ ለማስቆም አጎራባች አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ እንዲካተቱና፤ ነዋሪው መሬቱንም አስከብሮ የከተማው መሰረተ ልማትና አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆን፤ የሚለው የከተማ ልማት ጥናት ሲቀርብ፤ እነዚህ ሙሰኛ የመሬት ነጋዴ ባለስልጣናትና ባለሃብቶች፤ እንዴት የኦሮሚያን ወጣት በውሸት "መሬትህን ሊዘርፉ ነው" ብለው እንዳነሳሱት ዝርዝር መረጃው በጌታቸው ቢሮ ለሃይለማርያም ደሳለኝ ቀርቦ ነበር::

… ዋናዎቹ የኦሮሚያን መሬት ከባለሃብቶች ጋር ተቆራኝተው ሲዘርፉ ሲቸበችቡ የነበሩት እነ አባዱላ ገመዳ ለማ መገርሳ አብይ አሕመድና ሌሎች ባለስልጣናት ተመልሰው፤ እነሱው መሬትህን ሊዘርፉህ ነው ብለው ሕዝቡን ለአመፅ አነሳሱት:: እነዚህ ባለስልጣናትና ባለሃብቶች እየሰሩት የነበረውን ደባ እና መንግስት እርምት እንዲያደርግ በወቅቱ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ዝርዝር መረጃው ቢቀርብም፤ ሃይለማርያም ደሳለኝ የጀነራል ሳሞራ የኑስን ድጋፍ ተገን እድርጎ፤ ከእነ አብይ አሕመድም ጋር በነበረው ግንኙነት፤ በእነ ጌታቸው የመረጃና ደሕንነት ተቋም ተጠንቶ የቀረበውን ዝርዝር መረጃውን አሳልፎ ለወንጀለኞቹ ለእነ አብይ ሰጣቸው::

.... በዚህም ሂደት ነበር፤ እነዚህ ሙሰኛና ተባባሪ ሃይሎች በቅንጅት ሁለት ስለት ያለው ጦር መዘው፤ በአንድ በኩል የኦሮሚያን ወጣት "መሬትህን ተዘረፍክ" ብለው በማነሳሳት፤ በሌላ በኩል የመንግስትን ጦርና የኦሮሚያን ልዩ ሃይል በወጣቱ ላይ በማዝመት፤ በርካታ የኦሮሚያ ወጣቶችን ህይወት የቀጠፉት::

… ከኤርትራው አሸባሪም ሆነ ከሶማሊያው አልሸባብ ወይም ከቀይባሕር ማዶ የታሰቡም ሆነ የተጠነሰሱ ጥቃቶችን፣ አሻጥርና ደባዎችን አነፍንፎም ሆነ የመገናኛ አውታራቸውን ሰብሮ ገብቶ በመጥለፍ፤ መረጃን በወቅቱ ያስገኝ የነበረው የእነ ጌታቸው የመረጃና ደሕንነት ተቋም ነበር፡፡ እነዚህንም መረጃዎች በወቅቱ ሃገር ይመራሉ ለተባሉት ባለሥልጣናትና ተቋማት ለተግባራዊ እርምጃ ያቀርብ ነበር፡፡ ከመከላካያና ከፖሊስ ጋር በቅንጅትም በሃገሪቱ የፀረሽብር ግብረሃይል ውስጥ በመሳተፍ ለግብረሃይሉ በቂና ወቅታዊ የመረጃ ድጋፍ ያደርግ ነበር፡፡ በመሆኑም ነበር ባለፉት ከሃያ ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ጠላቶች የታሰበም ሆነ የተጠነሰሰ አንድም ጥቃት ከታሰበለት የጥፋት ቦታ ሳይደርስና ሳይፈፀም ከወዲሁ ማጨናገፍ የተቻለው፡፡

... በዚህም ሂደት የሰብኣዊ መብት ጥሰት አልተፈፀመም ማለት አይደለም:: ለበርካታ የኢህአዴግ መንግስት የስልጣን ዓመታት በግልፅ እንደሚታወቀው፤ የማሰርና የመመርመር ሙሉ ስልጣንና ሃላፊነት ኖሮት፤ ሲያስርና ሲመረምር የነበረው፤ በአቶ ወርቅነህ ገበየሁ የሚመራው መንግስታዊ መዋቅር ነበር:: የመረጃና ደሕንነት ተቋም ከዚህ የወርቅነህ ገበየሁ ተቋም ጋር የነበረው ግንኙነት መረጃዎችን አስሶ አጠናቅሮ ማቅረብ ብቻ ነበር:: በመንግስት የመቋቋሚያ አዋጅና መመሪያዎች መሰረት ሁሉም እስር ቤቶች ይተዳደሩ የነበሩት በወርቅነህ ገበየሁ ተቋም እንጂ፤ በመረጃና ደሕንነት ተቋም አልነበረም:: በመሆኑም በመረጃና ደሕንነት ተቋም ወይም ሃላፊዎችና ሰራተኞች የተፈፀመ እስራትም ሆነ ምርመራ አልነበረም::

… እነ አብይ አሕመድና ጓደኞቹ ስልጣን ከመቆጣጠራቸው በፊት ከውጭ ሃይላት ጋር በጥቅም ተሳስረው የኢትዮጵያን ጥቅምና ሉዓላዊነት ለባዕድ አሳልፎ በመሸጥ እየፈፀሙ የነበረውን የሃገር ክህደት በጥብቅ ተከታትሎ፤ ከግንቦት ሰባት ኢሳት ከኤርትራው የሃገራዊ ደሕንነት ተቋምና እስከ ግብፅ የዘለቀ የነበራቸውን ትስስር ጭብጥ መረጃዎችን በማሰባሰብ፤ በወቅቱ ሃገር ይመራሉ ለተባሉት በተለይም ለሃይለማርያም ደሳለኝና ለምክትሉ ደመቀ መኮንን በዝርዝር የሰነድና የድምፅ ማስረጃ አሳውቆ፤ ከወዲሁ እርምት እንዲወሰድ አበክሮ አሳስቦ ነበር:: ይህም አለመተግበሩ ብቻም ሳይሆን መረጃው ለወንጀለኞቹ እነ አብይ በእነ ሃይለማርያም በኩል እንዲደርሳቸው ተደረገ::

... በዚህ ሂደት መሃል ነበር የመረጃና ደሕንነት ተቋም በራሱ አፈፃፀም የኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ደሕንነት ለማስጠበቅ፤ ጌታቸው እራሱ የመሪ ተዋናይ ሚና የተጫወተበት፣ ሶስት ክፍላተ ኣህጉር ከአውሮፓ ኤሽያና ኣፍሪካን ያዳረሰ፤ በመጨረሻም ታርጌቱ አንዳርጋቸው ፅጌን ከየመን ኤርፖርት ከእነ ላፕቶፑና ዝርዝር መረጃዎቹ አሽገው አንጠልጥለው አዲስ አበባ ያስገቡት::

... የመረጃና ደሕንነት ተቋም በራሱ አፈፃፀም የኢትዮጵያን ሕዝቦቿን ደሕንነትና ጥቅሞች ለማስጠበቅ፤ ከኤርትራ የስለላና ወተሃደራዊ ተቋማት ውስጥ ዘለቆ በመግባት፣ በኤርትራ ተሰማርተው የነበሩ ኢትዮጵያን ለማጥቃት የታጠቁ ታቃዋሚዎችን በማተራመስ እርባና ቢስ በማድረግ፤ በመጨረሻም በሞላ አስገዶም ይመራ የነበረውን በሺዎች የዲምህት አመራርና ሰራዊት ከኤርትራ የወታደራዊና ሲቪል ስለላ ሰንሰለት አሾልኮ፣ ተታኩሶ ወደሃገሩ እንዲገባ ማድረጉ የሚታወቅ ነው:: ይህንን ሃገራዊ ጀብድ፤ የጌታቸው መረጃና ደሕንነት ተቋም ሙሉ ተውኔቱን ከጥንስሱ እስከ ፍፃሜው ስላስተባበረ፤ "የጎረቤት አገር ኤርትራን በመሰለል" በሚል "ወንጀል" በእነ አብይ አሕመድ ክስ ተመስርቶባቸዋል::

… የጌታቸው መረጃና ደሕንነት ተቋም ሃገራዊና ሕዝባዊ ገድል በርካታ መፃሕፍት ይወጣዋል:: ስለዚህ የሃገርና የወገን ባለውለታው ጌታቸው አሰፋ እየተፈለገ ያለው በባለዶሴዎቹ ወንጀለኛ ከሃዲ ተፈላጊዎች ነው፡፡ በኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ላይ በተለያየ መልክ፣ ቁመናና ይዘት ወንጀልና ክህደት የፈፀሙ፤ ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ መንግስታትና ተቋማት ናቸው፤ ነገሩ ጩኸቴን ቀሙኝ ሆኖ ተፈላጊዎቹ ፈላጊ የሆኑት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም እውነታው እስኪገለጥለት ድረስ፤ በመንጋ ሆይ ሆይታ ከባለዶሴዎች ጋር ተድሮ፤ ሰርግና ምላሽ እያለ፤ ዶሴኛው ባለውለታውንና የስራ ባልደረቦቹን እንደወንጀለኛ እያንጓጠጠ፤ የውድቀትና ዕልቂት፤ የመተራመስና መበታተን ቁልቁለቱን ተያይዞታል፡፡

… ይህን የኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ሰላም፣ መረጋጋት፣ ደሕንነት፣ ልማትና ዕድገት ለረዥም ዓመታት ያስከበረና ያስጠበቀ ተቋምና የዳበረ የሰው ሃይል በመናድ፤ ከኢሳያስ አፈወርቅና አምሳያዎቹ ጋር እየታየ ያለው ሽርጉድና መራወጥ እየታዘበ ያለ ማንኛውም ሃገሬን እወዳለሁ የሚል ዜጋ፤ ምናልባትም ‘ይህችን ሃገር እንደሃገር ለመበታተን የተጎነጎነ ሸር ስለአለመኖሩ ምን ዋስትና አለ?’ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ለማንኛውም እስኪ ግዜና ሂደት እራሱ መልሱን ይመልሰው...» ሕዳር 21 ቀን 2011 ዓ.ም

የወዳጄ መግለጫ ጥልቅና ሰፊ ነው፡፡ ሁሉንም ለማቅረብ ይከብደኛል ብቻም ሳይሆን፤ ወዳጄም ከዚህ በላይ እንዳካፍላችሁ አልፈቀደልኝም፡፡

ስለ አሁኑ የትግራይ ማእከላዊ ኮማንድ ከፍተኛ አመራር ታጋይ ጌታቸው አሰፋ ወቅታዊ ትዝብትና፤ ሰሞኑን በእሱ ላይ ስለተላለፈው «ፍርድ» በቀጣይ በሌላ ሓተታ ጠብቁ::

ትግራይ ትስዕር ኣላ! ካሳ ሃይለማርያም