ስለአቶ ጌታቸው አሰፋ በተለይም ለኢትዮጵያውያን የቀረበ፤ ተጋሩ ስለሚያውቁት ነው!
ብ Kassa HaileMariam
***********************************
ኢትዮጵያውያን ከ«ሙሴ» ጋር ተሞሽረው ሰርግና መልስ ላይ በነበሩበት ወቅት፤ በሕዳር ወር 2011 ዓ.ም ስለጌታቸው አሰፋ እውነታውን ገልፀንላቸው ነበር! በዚህ ተከታታይ ፅሑፍ በክፍል አንድና ሁለት ይቀርባል:: ኢትዮጵያውያን እስኪ በዛሬው ሁኔታችሁ ላይ ሆናችሁ፤ ሰከን ብላችሁ ይህንን ከሶስት ዓመት በፊት ያልናችሁን አጣቅሳችሁ አንብቡት፤ ተነጋገሩበት ከአረንቋ ለመውጣት ይጠቅማችኋልና፡፡ ከዚያም በክፍል ሶስት፤ ስለአሁኑ የትግራይ ማእከላዊ ኮማንድ ኣባል ታጋይ ጌታቸው፤ እንዲሁም የኣብይ ኣሕመድ መንግስት በጌታቸውና በነበር የስራ ባልደረቦቹ ላይ፤ በዚህ ወቅት ለምን ተጣድፎ «የፍርድ» ውሳኔ አስተላለፈ፤ በዝርዝር እንመለከተዋለን፡፡
ክፍል አንድ
በአሁኑ ወቅት የትግራይ ማእከላዊ ኮማንድ ኣባል፤ የቀድሞው የኢትዮጵያ የብሄራዊ መረጃና ደሕንነት አገልግሎት ዋና ዳይረክተር፤ አቶ ጌታቸው አሰፋ ለምን በጥብቅ ተፈላጊ ሰው ሆነ?
«በባለስልጣናትና በባለሃብቶች፣ በሃገር ውስጥና በውጭ ሃይሎች ጌታቸው አሰፋ በጥብቅ ይፈለጋል፡፡ ይህ ሰው እንዲህ ተፈላጊ የሆነበትን ሚስጥር የኢትዮጵያ ሕዝብ በውል አያውቀውም» ሲል ያጫወተኝ ስለጌታቸው በቅርብ የሚያውቅ አንድ ወዳጄ ነው፡፡ «እንዴት?» ስል ላቀረብኩለት የአግራሞት ጥያቄዬ ያጫወተኝን ነው እንደሚከተለው ላጋራችሁ የፈቀድኩት፡፡
ወዳጄ፤ «መጀመርያ ይህንን አዋጅ አንብበው» ብሎ የጌታቸው አሰፋ የቀድሞ መስሪያቤት ‘የብሔራዊ መረጃና ደሕንነት አገልግሎት’ የተቋቋመበትንና የተመራበትን ይህንን ያያዝኩትን አዋጅ ሰጠኝ፡፡ ከአናት እስከ እግርጌው አነበብኩት፡፡ እናንተም አንብቡት፤ ወዳጄ ጥያቄ ስላለው፡፡
«አነበብከው?» አለኝ፡፡ «አዎ» አልኩት፡፡ «በደንብ አነበብከው?» አለኝ ደግሞ፤ ተከታዩን ጥያቄውን ለማስከተል አዋጁን አድቅቄ ስለመገንዘቤ ማረጋገጫ ፈልጓል፡፡ «አዎ በዝርዝር አንቀፅ በአንቀፅ እስከ ንዑስ አንቀፅ አንብቤዋለሁ» አልኩት፡፡
«ጥሩ፡፡ እንግዲያው የ‘ዶሴኛው’ ጌታቸው ስልጣንና ሃላፊነት፣ ያለፉት በርካታ ዓመታት ተግባራቱም በዚህ አዋጅ መሰረት የኢትዮጵያን ሰላምና መረጋጋት ማረጋገጥ፣ ልማትና ዕድገቷን ማስቀጠል፣ የውስጥና የውጭ ሃይሎችን ጥቃትና ስጋቶችን ከወዲሁ በመረጃ አስደግፎ ተከታትሎ ለማክሸፍ የሚያስችል መረጃ ለመንግስት የበላይ አስፈፃሚ አካል ማቅረብ፣ የሃገሪቱና ሕዝቦቿ ዕኩልነት መከበሩንና የአብሮነት አንድነት ማስቀጠል፣ እንዲሁም የኢኮኖሚና የተለያዩ ማሕበራዊ አገልግሎቶች አሻጥሮችን በመከታተል መረጃ ለአስፈፃሚው አካል ማቅረብ የመሳሰሉ ተግባራትን ሲከውን ነው የኖረው…» እያለ ወዳጄ በተመስጦ ገለፃውን ቀጠለ፡፡
«ምን እያልከኝ ነው? ይህን ያህል ለወገንና ለሃገር የሚበጅ ለበጎ ተግባር የተሰማራ ዜጋ ከነበር፤ አሁን ለምን ይህን ያህል በ‘ወንጀል’ ተፈላጊ ሆነ?» ብዬ አቋረጥኩት፡፡
«ቆይ! ለምን እንደሚፈለግ እነግርሃለሁ፤ አታቋርጠኝ» አለኝ፡፡ ስላቋረጥኩት ደስተኛ እንዳልሆነ ከገፅታው ስለተገነዘብኩ ሐሳቡን እስከሚያጠቃልል በዝምታ ላዳምጠው ወሰንኩ፡፡ ጊዜ ወስዶ በስፋትና በዝርዝር ካጫወተኝ ውስጥ ከፊሉን ላካፍላችሁ፡፡
… የጌታቸው አሰፋና ጓደኞቹ በአጠቃላይ የአገልግሎት መስሪያቤቱ ያለፉት በርካታ ዓመታት ዋና ተግባርና ዓላማ በአዋጁ አንቀፅ ስድስት ላይ እንደተመለከተው ተኣማኒነት ያለው መረጃ ለሃገሪቱ የበላይ አስፈፃሚ አካል ማለትም ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚመሩት የሃገሪቱ የብሔራዊ ፀጥታ ምክርቤት (National Security Council) በወቅቱ በማቅረብ ሕዝቦቿ አስተማማኝ ደህንነት እንዲኖራቸው፤ የሃገሪቱም ብሔራዊ ደሕንነት እንዲጠበቅ ማድረግ ነበር፡፡ በዚህም ሃገራዊና ሕዝባዊ ግዳጃቸውን በአግባቡ ስለመወጣታቸው ያለፉት በርካታ ዓመታት የሃገራችን ሰላምና መረጋጋት፣ ልማትና ዕድገት ታሪካዊ እማኞች ናቸው፡፡
… ኢትዮጵያ ያለችበት መልክአምድራዊ አቀማመጥ እጅግ ውስብስብ፣ የበርካታ ሃያላን የዓለማችን መንግስታት የዓለምአቀፍ የባሕር መስመሮች ላይ ያላቸውን ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር የሚራኮቱበትና፣ አሉ የተባሉ የመረጃና የደሕንነት መዋቅሮቻቸውን ዘርግተው የእያንዳንዳቸውን የመረጃ ፍልሰት ለመሰለልና በልጦ ተጠቃሚ ለመሆን ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ፣ የስላላ ባለሙያዎችንና መገልገያ መሳሪያዎችን ያሰማሩበት ቀጠና ነው፡፡ በባሕር መስመር ላይ ይህን የባሕር ቀጠና የሚመስሉ መራኮቶች ያሉበት አካባቢ ቢኖርም እንደዚህ የቀይ ባሕርና የሕንድ ውቅያኖስ ቀጠና የተወሳሰበ አካባቢ በሌላው የአለማችን ክፍል የለም፡፡
… በተለይም የአፍሪካ ቀንድ የቀይ ባሕር ቀጠና፤ በአካባቢው ካሉ የአፍሪካ ቀንድ አፍሪካውያን አገሮችና ከቀይ ባሕር ማዶ ከሚገኙት በርካታ የዓረብ ሃገራት አልፎ ሁሉም ታላላቅና ሃያላን የሚባሉ አገሮች፤ ማለትም አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩስያ፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ እስራኤል፣ ቱርክ፣ ኢራንና ሌሎች በርካታ የአውሮፓና የኤዥያ አገሮች እጃቸውን በቀጥታና በተዘዋዋሪ ያስገቡበትና የከረረ ውዝግብ ተለይቶት የማያውቅ ቀጠና ነው፡፡
… እንግዲህ በታሪኳ፣ በአቀማመጧ፣ በሕዝብ ብዛትና በሌሎች በርካታ መለኪያዎች የገዘፈችው የዚህ ቀጠና ሃገር ኢትዮጵያ በእነዚህ ሃይሎች ሁሉ ትብብሯ ተፈላጊና ወሳኝ ነው፡፡ ምንም እንኳን የባሕር በር ባይኖራትም ይህንን ቀጠና ለመቆጣጠርና ጥቅሙን በበላይነት ለማስጠበቅ የሚሯሯጥ ማንኛውም ሃገር የኢትዮጵያ አስፈላጊነት ወሳኝ ነበር፡፡ ይህም ተፈላጊነት ይበልጥ ጎልቶና ለውድድር ቀርቦ የነበረው ባለፉት ሃያ ዓመታት ዓለማችን በሽብር ይበልጥ ታውካ በነበረበት ዘመን ነው፡፡
… በመሆኑም ነበር ከማንኛውም የኢትዮጵያ ባላስልጣን ይልቅ የጌታቸው አሰፋ ትብብር በእነዚህ በርካታ መንግስታትና የመረጃና የደሕንነት ተቋማት ተፈላጊነቱ እጅግ የላቀ የነበረው፡፡ በመሆኑም ነው ጌታቸው በሃገራችን ታሪክ ውስጥ ለወደፊቱ በወርቅ ቀለም ሊፃፍ የሚችል፤ የሃገራችንን ሰላም ደህንነት ከማረጋገጥ አልፎ፣ የሃገራችንን ዓለምአቀፋዊ ጥቅሞች በማስከበር፣ ከውስጥም ሆነ ከውጭ የተቃጡም ሆነ የታሰቡ ጥቃቶችን ከወዲሁ እንዲቀጩ በማድረግ፣ ከጎሬበት ሃገራት አልፎ ከበርካቶቹ መንግስታት ጋር የጋራ ትብብር በማድረግ የቀጠናውን መረጋጋትና ደህንነት አስተማማኝ በማድረግ፣ በማስተባበርና በአመራር የአንበሳውን ድርሻ የተጫወተ ኢትዮጵያዊ ጀግና ነው፡፡ ይህ ተግባሩም ከሞሳድና ሲኣይኤ አንስቶ በበርካቶቹ የአለማችን የመረጃና የደህንነት ተቋማት መዛግብት ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
… በመሆኑም ነበር በተለይም ባለፉት 17 ዓመታት ኢትዮጵያ በታሪኳ ትውልድን እጅግ በሚያኮራ መልኩ በምዕራቡም ሆነ በምስራቁ፣ በአደጉትም ሆነ በታዳጊ፤ በአብዛኞቹ የምድራችን ሃገራት ከፍተኛ ከበሬታና የላቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፤ ከዚህም አልፎ በርካታ የየሃገራቱ ባላሃብቶችና መንግስታት በብዛት መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ በሃገሪቱ ልማት ውስጥ መሳተፍ ጀምረው የነበረው፡፡ በመሆኑም ነበር ከዓለምአቀፍ የፋይናንስ ተቋማት አልፎ በርካታ መንግስታት የዕርዳታና የብድር ገንዘብ በብዛት ያፈሰሱልንና ከዚህም አልፎ ጂ8 እና ጂ20 እንዲሁም ህንድ ባለሃብትና የበለፀጉ አጋሮች በተመሳሳይ በሁሉም የምክክር ስብሰባዎቻቸው ውስጥ ኢትዮጵያ ልዩ ቦታ አግኝታ በድምፅ ለዓመታት ተሳታፊ የነበረችው፡፡
… ኢትዮጵያ በተለይም ባለፉት 17 ዓመታት ከገነባችው የተሟላ ወታደራዊ የመከላከያ ተቋም ጀርባ በዓለምአቀፍ ፀረ-ሽብር ዘመቻና ሰላም ማስከበር ዘመቻ ውስጥ በጌታቸው አሰፋ የተመራው የብሔራዊ መረጃና ደሕንነት መስሪያቤት አሻራ ያላረፈበት ሂደት የለም፡፡ በተለይም ያለንበት ቀጠና ከዋናው የፀረ-ሽብር ትግሉ እምብርት የመካከለኛው ምስራቅ ጋር ያለው የቀረበ አቀማመጥና ተያያዥነት አኳያ የሃገራችንን ደህንነቷንና ሙሉ ጥቅሟን ከማስጠበቅና ማረጋገጥ ተቀዳሚ ተግባር አንስቶ፤ የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት በማስከበር ጉልሕ ታሪክ ተሰርቷል፡፡
… እንግዲህ ይህን ያህል ስፋትና ጥልቀት ባለው፤ በርካታ ባለጉዳይ መንግስታትንና ዓለምአቀፍ የመረጃና ደሕንነት ተቋማት፣ እንዲሁም የፀጥታውን ምክርቤት ጨምሮ በርካታ ዓለምአቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በሚያጅቡት በእንደዚህ ያለ ውስብስብ ቀጠና ውስጥ በአመራር ለዚያውም በብዙዎች ዘንድ ትብብርህ በሚፈለግበት አመራር ላይ መቀመጥ፤ ሲበዛ ብልሃትን አዋቂነትንና ቆራጥነትን የሚጠይቅ ግዙፍ ሃላፊነት መሆኑነ ለመገንዘብ አይከብድም፡፡ ይህንን የገዘፈ ሃላፊነት ነው ጌታቸው አሰፋ በአግባቡ በመወጣት ሃገራችንና ሕዝቦቻችን በበርካታ የዲፕሎማሲ መድረኮች ተከብረው፣ ጥቅሞቻችን ተጠብቀው፣ ሰላምና መረጋጋት ተረጋግጦ፣ መላው የሕዝቦች አስተሳስብ ለልማትና ዕድገት ተነሳስቶ ተሰማርቶ የነበረው፡፡ ይህንን ሐቅ ማንኛውም አገሩን የሚወድ ዜጋ መለስ ብሎ ያለፉትን በርካታ ዓመታት በማስታወስ ሊገነዘበው ይችላል፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት የጌታቸው አሰፋ እጅ ከማንም የኢትዮጵያ ባለስልጣን፤ ከአቶ መለስ ዜናዊም በላይ ልቆ ጉልህ አስተዋፅዖ አበርክቷል፡፡
… ከጎረቤት ሃገራት ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ሱማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን አልፎ በግብፅና በእያንዳንዳቸው የመካከለኛው ምስራቅ ዓረብ አገሮች ውስጥ ድረስ የረዘመ የጠለቀ ስራ ተሰርቷል፡፡ በመሆኑም በሃገራችን ላይ ከተቃጡትና ከታሰቡት ባሻገር የባሕር ላይ ውምብድናና ዓለምአቀፍ የሽብር ጥንስሶችን በማምከን በመመከትና በማጨናገፍ ረገድ በርካታ አመርቂ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ በአብዛኞቹም ጌታቸው አሰፋ የሚመራው ኢትዮጵያዊው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መስሪያ ቤት አሻራውን አሳርፏል፡፡
… የጌታቸው አባት ሻምበል ኣሰፋ የደርግ ቀይሽብር ሰለባ ናቸው፡፡ የደርግ ፋሽዝም መገለጫ በሆነ አሰቃቂ ሁኔታ ሃገራቸውን በታማኝነትና በቅንነት ስላገለገሉ ብቻ ከመሰቃየታቸውም አልፎ እጅግ አረመኔያዊ በሆነ መንገድ በሰንሰለት ታስረው እንዳሉ ነው ተረሽነው ሬሳቸው በመቐለ አውራ መንገድ ላይ ተዘርግቶ የዋለው፡፡ ይህ የደርጎች ተግባር ግን እንኳንስ የጌታቸውን ሞራል ሊነካ በዓስር ሺዎች ጀግኖችን ነበር ያፈራው፡፡ በመሆኑም ነበር ከተራ ታጋይነት አንስቶ እስከ ከፍተኛ አመራርና ኮሚሳር በመሆን በትጥቅ ትግሉ ወቅት አንፀባራቂ ገድል ከፈፀሙ ብርቅዬ የትግራይ ታጋዮች ተርታ በግንባር ቀደምትነት ከሚወሱት አንዱ ጌታቸው የሆነው፡፡ በመሆኑም ነበር የሃገርን ሰላምና ደህንነት በማስከበር ረገድ ጌታቸው ከአመራርና የስራ ጓዶቹ ጋር በመሆን ማንም የማይወዳደረውን የላቀና የአንበሳውን ድርሻ የተጫወተው…»
ወዳጄ እነደዚህ እያለ ስለ ጌታቸውና ዝርዝር ስራዎቹ በስፋት ጨዋታውን ቀጠለ፡፡ ሁሉንም በዚህ ፅሑፍ በአደባባይ መዘርዘር ይከብዳል፡፡ ተነግሮ ተዝቆ የማያልቅ ሃገራዊ ገድል፣ እጅግ ግዙፍ ክብር ያለው የሃገርና የህዝብ ባለውለታ ብዬ ባልፈው ይበቃል፡፡ የግለሰብ አመራርና ገድል ቢሆንም የሃገርና የሕዝብ ክቡር ታሪክ ነውና ወቅቱን ጠብቆ አንድ ሳይሆን በርካታ መፃሕፍት የሚከተቡበት የወርቃማ ትውልድ ወርቃማ ታሪክ ነው፡፡
አላስችል አለኝና የወዳጄን ስፋት ያለው ጥልቅና የተወሳሰበ ሐተታ እኔ ነኝ ያቋረጥኩት፡፡ «አንድም ይህን ያህል ሃገራዊ ገድል የፈፀመ፤ በግንባር ቀደምትነት በአመራር የአገሩንና የሕዝቦችን ሰላምና ፀጥታ፣ አንድነት፣ ደህንነትና ጥቅሞች ያስጠበቀና ያስከበረ ዜጋ ከሆነ፤ እንዴትና ለምን በወንጀል ተፈላጊ ሆነ? ደግሞስ ‘ዶሴኛው’ ጌታቸው የተባለበት ስያሜ ትርጉሙ ምንድነው?...» በማለት ነበር ወዳጄን ያቋረጥኩት፡፡ መልሱም፤ ይቀጥላል
ትግራይ ትስዕር ኣላ! ካሳ ሃይለማርያም
|